የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በሌላ ዙር ጉዞ ሐሙስ ዕለት ለጉብኝት ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተዘገበ።

አንድ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ፌልትማን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመወያየት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ግጭት ለማብቃት ግፊት ያደርጋሉ ተብሏል። አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ደም አፋሻሽ ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት እንዲያግዙ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሰየሙት ጄፍሪ ፌልትማን ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያና ወደ አካባቢው አገራት መመላለሳቸው ይታወሳል።

ሐሙስ ታኅሣሥ 28/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ የሚገቡት ፌልትማን “የሰላም ንግግርን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር” እንደሚወያዩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ከፍተኛ ኃላፊው መናገራቸው ተዘግቧል። ጦርነቱ በተባባሰበትና የህወሓት ኃይሎች ግስጋሴ በተጠናከረበት ጊዜ ቱርክንና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ ወደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ግብፅ በተደጋጋሚ የተመላለሱት ጄፍሪ ፌልትማን መንግሥትና አማጺያኑ ለንግግር እንዲቀመጡ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ወደ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ የተመላላሱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባሻገር ከህወሓት ተወካዮች ጋር ኬንያ ውስጥ መነጋገራቸውን ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር። በተጨማሪም ፌልትማን ከአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት እንዲሁም ለጦርነቱ መፍትሔ ለማፈላለግ ሕብረቱ ከሰየማቸው ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋርም መመካከራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል።

ከመልዕክተኛው በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ግጭት እንዲቆምና ለጦርነቱ በድርድር ላይ የተመሰረተ መፍትሔ እንዲገኝ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን ጫናን የሚያሳድሩ ያሏቸውን እርምጃዎችንም መውሰዳቸው ይታወቃል። ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አንስቶ ተግባራዊ የሚሆነው ኢትዮጵያን የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ተጠቃሚነት የሚያግደው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውሳኔም አንዱ ነው።

ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት ሳቢያ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔን ለማስገኘት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የህወሓት ኃይሎች ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወዲህ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመግባታቸው የተባባሰው ጦርነት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ተባብሶ ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ በመሻገር፣ ወደ ሰሜን ሸዋ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል።

ካለፈው ኅዳር ወር ወዲህ ግን መንግሥት ባካሄዳቸው ከፍተኛ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎች በህወሓት ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ የቻለ ሲሆን፣ የቡድኑ መሪዎች ግን ከአካባቢው የለቀቁት በስልታዊ ውሳኔ ነው ሲሉ ቆይተዋል። በማስከተልም የህወሓት መሪዎች ኃይሎቻቸውን ከአፋርና ከአማራ ክልል ያስወጡት ለሰላማዊ መፍትሔ እድል ለመስጠት መሆኑን በመግለጽ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ጽፈዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም አማጺያኑ ከአማራና ከአፋር ክልሎች የወጡት ከባድ ወታደራዊ ሽንፈት ስላጋጠማቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ሠራዊቱ ለጊዜው የህወሓት ኃይሎችን ለመምታት ወደ ትግራይ ክልል እንደማይገባ ገልጿል። ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ከህወሓት ኃይሎች ከአማራና ከአፋር ክልል መውጣታቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ዘመቻውን ወደ ትግራይ ላለመቀጠል መወሰኑ ለሰላም በር ይከፍታል ብለው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ጦርነት እየተካሄደ ስለመሆኑ በይፋ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳሉ ይነገራል።

ምንጭ – ቢቢሲ