በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረ ታጣቂ ቡድን የቀድሞ መሪ ታስሮበት ከነበረ የአሶሳ ከተማ እስር ቤት ማምለጡን አንድ የክልሉ ከፍተኛ የፀጥታ ኃላፊ ለቢቢሲ አረጋገጡ።

የቤንሻጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) የተባለው ታጣቂ ቡድን የቀድሞ መሪ የነበረው አብዱልዋህብ መሐዲ ከእስር ቤት ያመለጠው ከሳምንት በፊት እንደሆነ የክልሉ ፀጥታና ደኅንነት ግንባታ ኃላፊ አቶ ጋሹ ጋውዝ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ኃላፊው አብዱልዋህብ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥሮ ረዥም ጊዜ በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤት ታስሮ የነበረ ታራሚ መሆኑን አመልክተው፤ በቅርቡም ግለሰቡ በጠየቀው ይግባኝ መሠረት ታማኝ እስረኛ ሆኖ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ውስጥ ሲሳተፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

“ታማኝ እስረኛ ነው፤ የውሳኔ ጊዜውን እየጨረሰ ነው በሚል በተፈጠረ መዘናጋት ምክንያት ነው አምልጦ የሄደው” ያሉት ኃላፊው እስረኛው እንዲያመልጥ ያስቻለውን አጋጣሚ እንዲፈጠር ባደረጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ “በቀጣይ የሚታይ መሆኑን” ገልጸዋል። ከእስር ቤት ያመለጠው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ የማይታወቅ ሲሆን ምናልባትም ድንበር ተሻግሮ ወደ ሱዳን ሊገባ እንደሚችል ተጠርጥሯል።

አቶ ጋሹ ጋውዝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፀጥታ ኃይሎችግ ከእስር ያመለጠውን አብዱልዋህብ ለመያዝ ክትትል እያደረጉ ሲሆን ድንበር ቢሻገር እንኳን በሱዳን መንግሥት ቁጥጥር ስር መግባቱ እንደማይቀር ተናግረዋል። ለዚህም በቅርብ ጊዜ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ተዋሳኙ የሱዳን ግዛት አስተዳዳሪዎች በሁለቱም በኩል ያለውን የፀጥታ ስጋት በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት አሶሳ ላይ ተገናኝተው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማስታወስ፤ ተፈላጊው ሱዳን ቢገባም ማምለጥ እንደማይችል አብራርተዋል።

“ሱዳን ውስጥ የሚፈለግ ወንጀለኛ ካለ አሳልፈው ለመስጠት፤ ሱዳን የምትፈልገው ወንጀለኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለም ለማስረከብ የጋራ ስምምነት አለን” ብለዋል ኃላፊው። የቤንሻጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ታጣቂ ቡድን የቀድሞ መሪ የነበረው አብዱልዋህብ መሐዲ በተለያዩ ጊዜያት እስከ እድሜ ልክ አስራት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ ከአስር ቤት ሲያመልጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአስር ዓመት በፊት እንዲሁ ከእስር ያመለጠ ሲሆን ከዚያ በኋላም ከአማጺያን ጋር ተቀላቅሎ በሱዳንና ኢትዮጵያ አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በመሆን የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከዓመታት በፊት የክልሉ መንግሥት እና የፈደራሉ መንግሥት ለታጣቂ ቡድኖች ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሶ በተለያዩ ሥራዎች ላይ መቆየቱ ተነግሯል። አቶ አብዱልዋህብ በአሶሳ ዞን ማረሚያ 4 ዓመት ከቆየ በኃላ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ረፋድ ማምለጡን እና ክትትል እየተደረገበት መሆኑን የክልሉ የጸጥታ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

አብዱልዋሃብ መሐዲ በድጋሚ ለእስር የተዳረገው ከዓመታት በፊት በአሶሳ ከተማ በተከሰተ አለመረጋጋት በርካታ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በግጭቱ ተሳትፎ እንዳለው ተጠርጥሮ ነበር። ከዚህም በኋላ ለአራት ዓመታት ያህል በአሶሳ ማረሚያ ቤት ውስጥ በእስር ከቆየ በኋላ የቅጣት ጊዜው እየተጠናቀቀ ባለበት ጊዜ ነው እንዳመለጠ የተነገረው። ከሱዳን ጋር የሚዋሰነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጠቂ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ለበርካታ ሰዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።

የክልሉ መንግሥትና የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆምና ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር የተለየ የዕዝ ማዕከል (ኮምንድ ፖስት) አቋቁመው እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ