በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ወረርሽኙ መገኘቱን የተደረጉ የምርመራ ውጤቶች አመለከቱ።

ካለፈው ሰኞ አስከ ትናንት እሁት ድረስ ባለፉት ሰባት ቀናት በ77,083 ናሙናዎች ላይ በተደረጉ ምርመራዎች በ22,321ዱ ላይ ቫይሱ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ የሚያወጣቸው የወረርሽኙ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ይህም አስካሁን በአንድ ሳምንት ከተመዘገቡ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሚኒስቴሩ እንዳለው እየተመዘገበ ያለው የበሽታው የመስፋፋት መጠን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ቀደም ሲል በነበሩ ሳምንታት ምርመራ ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል በየዕለቱ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ከአምስት መቶ በላይ፣ ነገር ግን አንድ ሺህ እንኳን የማይደርስ ነበር። ባለፈው ሳምንት ግን ሰኞ ዕለት ከተመዘገበው 681 ውጪ በሌሎቹ ቀናት አሃዙ ከፍተኛ ነበር። በዚህም መሠረት በየዕለቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በ2300 እና 5000 መካከል ይገኛል። ዝቅተኛው ማክሰኞ ዕለት የተመዘገበው 2,323 ሲሆን፣ ከፍተኛ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት 5,013 የተመዘገበው ሲሆን፣ በሳምንቱ ውስጥ በአጠቃላይ በ22,321 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

የወረርሽኙ ቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከሚመረመሩት ሰዎች ብዛት አንጻር ከፍና ዝቅ የሚል ቢሆንም ያለፈው ሳምንት አሃዝ ግን ከፍተኛ እንደሆነ ቀደም ካሉት ሳምንታት ጋር የተደረገው ንጽጽር ያመለክታል። ቀደም ሲል በነበረው ሳምንት ውስጥ ከተመረመሩ 53 ሺህ ሰዎች መካከል 8500 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የተመዘገበው ቁጥር ግን በእጅጉ ከፍተኛ ነው። በቀደሙት ሳምንታት ምርመራ ካደረጉ ሰዎች መካከል ሦስት በመቶ ያህሉ ላይ ብቻ የኮሮናቫይረስ ይገኝባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከአንድ ሳምንት በፊት ግን ቁጥሩ ወደ 28 በመቶ ከፍ ብሎ ነበር። ባለፈው ሳምንት ደግሞ በእጀጉ አሻቅቧል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት “እስካሁን የነበረው አካሄድ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ከታኅሣሥ 07/2014 ዓ. ም. ወዲህ ባሉት ቀናት በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” ብለዋል። ጨምረውም በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ምርመራ ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል “አንድ ሦስተኛው ቫይረሱ እየተገኘባቸው ስለሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መወሰድ አለበት። ለዚህም ማስክ በአግባቡ ማድረግና የመከላከያ ክትባት መውሰድ ይገባል” ሲሉ መክረዋል።

በበርካታ የዓለም አገራት መገኘቱ የተረጋገጠውና ከሰው ወደ ሰው የመዛመት አቅሙ ከፍተኛ የሆነው አዲሱ የኦሚክሮን ቫይረስ ዝርያ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አለመኖሩ ገና ያልተረጋገጠ ሲሆን ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል። “በሌሎች አገሮች የሚታየው የኦሚክሮን ዝርያ በኢትዮጵያም ምልክቶቹ ታይተዋል። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአስጊ ሁኔታ ጨምሯል። አሁን ናሙና እየመረመርን ነው። እስክናረጋግጥ ድረስ ኦሚክሮን መግባቱን ለመናገር አስቸጋሪ ነው” ብለዋል ዶ/ር ደረጄ።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ አስከ ትናንት ድረስ 4 ሚሊዮን 52ሺህ 568 ሰዎች ተመርምረው 400 ሺህ በሚጠጉት ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፣ 6 ሺህ 898 ደግሞ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል። በሽታውን ለመከላከል የሚረዳው ክትባት በአገሪቱ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተከተቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ሕዝብ አንጻር ይህ አሃዝ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል።

የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለመዱትን የመከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ ዘወትር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚመክሩት የጤና ሚኒትር ዲኤታው ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ክትባት መውሰድም አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጤና ሚኒስቴር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የጤና ባለሙያዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ክትባት እንዲወስዱ ማድረግ እና ያልተከተቡ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የመንግሥት የነጻ ሕክምና ተጠቃሚ እንይሆኑ እንደሚደረግ ጨምረው ገልጸዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ