የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ከህወሓት ኃይሎች ነጻ በማውጣት በቁጥጥሩ ስር ባስገባቸው የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎች ላይ እንዲቆይ መታዘዙ ተገለፀ።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል ቦታዎችን መልሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱ ዘመቻውን ወደ ትግራይ እንዳይቀጥል ሠራዊቱን ማዘዙን አስታወቋል። መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የነበረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ ቆይቷል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ ላይ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሠራዊቱ ለጊዜው ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ እንዳይገባ መወሰኑን አስረድተዋል። ባለፉት ሳምንታት የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊትና የአፋርና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር መቻላቸውን አስታውቀዋል።

‘ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት’ ተብሎ የተሰየመው ተልዕኮ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ በማውጣት የመጀመሪያውን ግቡን አሳክቶ መጠናቀቁን ዶ/ር ለገሰ ተናግረዋል። በዚህም ዘመቻ በአማጺያኑ ተይዘው የነበሩት የአፋርና የአማራ ምሥራቃዊ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ነጻ እንዲወጡ መደረጉንና መንግሥት ቡድኑ “ዳግም ለአገሪቱ ሰላም ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ የማድረስ አላማውን” ማሳካቱንም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ህወሓት ያለው “ፍላጎትና የማድረግ አቅም ክፉኛ ተመትቷል። ነገር ግን ዳግም ፍላጎቱ እንዳይቀሰቀስ መንግሥት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን እርምጃዎች በቀጣይነት የሚወስድ ይሆናል” ብለዋል። ሠራዊቱ በአማጺያኑ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ ቀጣይ ዙር ዘመቻ ወደ ትግራይ ክልል ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ መንግሥት ምክንያቶችን በማስቀመጥ ሠራዊቱ አሁን ባለባቸው ቦታዎች “ጸንቶ እንዲቆይ መታዘዙን” ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሠራዊቱ ከዚህ በፊት በትግራይ ውስጥ ያጋጠሙት ችግሮችና ጥቃቶች እንዳይገጥሙት ለማድረግና አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ በተጠና መልኩ ሠራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ ለማድረግ በማሰብ ውሳኔው መተላለፉን ተናግረዋል። በተጨማሪም ወደ ትግራይ የመንግሥት ሠራዊት የሚገባ ከሆነ “ህወሓት ካዘጋጀው የሴራ ወጥመድ ሠራዊቱንና መንግሥትን ለመከላከል” መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በጦርነቱ ወቅት የተገደሉ ተዋጊዎቹን የጅምላ መቃብሮችን በማዘጋጀት የዘር ጥፋት ተፈጽሟል የሚል ክስ ለማቅረብ ቡድኑ እየተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።

ነገር ግን የአገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ወደ ትግራይ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብትና ግዴታ አለበት በማለት ዶ/ር ለገሰ አስረድተዋል። ከቀናት በፊት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ የውጭ አገር አምባሳደሮች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ቡድንን ለማሳደድ ትግራይ ውስጥ ገብቶ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው ገልጸው ነበር።

ጨምረውም ከዚህ በኋላ ህወሓት ምንም አይነት ጥቃት ለመፈጸም እንዳይችል ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ መንግሥታቸው እንደሚያደርግ እና የአገሪቱን የግዛት አንድነት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ትግራይን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የፌደራሉን ሠራዊት የማሰማራት መብቱን እንደሚያስከብርም ተናግረዋል። ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትን እንዳስከተለ እየተነገረ ሲሆን ባለፉት ወራት ጦርነቱ የተካሄደባቸውና በአማጺያኑ ተይዘው በነበሩት የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ከባድ ውድመት መድረሱን ክልሎቹ አሳውቀዋል።

የህወሓት ኃይሎች ከዚህ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ወደ ሁለቱ ክልሎች ዘልቆ በመግባት በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር በአፋር በኩል የጂቡቲ ወደብን ከመሃል አገር ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ለመያዝ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ ለመገስገስ ውጊያዎችን ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። በተለይ ከኅዳር ወር አጋማሽ ወዲህ የፌደራል መንግሥቱ ከክልል ኃይሎች ጋር በመጣመር በወሰዳቸው ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃዎች፣ የህወሓት ኃይሎችን ግስጋሴ ከመግታት አልፎ ይዘዋቸው የነበሩ ቁልፍ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ችሏል።

ከቀናት በፊት ደግሞ የህወሓት መሪዎች ኃይሎቻቸውን ከአፋርና ከአማራ ክልል እያስወጡ ያሉት ለሰላማዊ መፍትሔ እድል ለመስጠት ነው ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከባድ ወታደራዊ ሽንፈት ስላጋጠማቸው መሆኑን ገልጿል።

ምንጭ – ቢቢሲ