የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ቡድንን ለማሳደድ ትግራይ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።
አምባሳደር ሬድዋን ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ አምባሳደሮች ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የህወሓት ተዋጊ ይዘዋቸው ከነበሩ አካባቢዎች የወጡት ለሰላም ካለው ፍላጎት ሳይሆን በተቃራኒ ከባድ ሽንፈት ገጥሟቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት “ሽብርተኛውን ቡድን ለማሳደድ በትግራይ ውስጥ በሚገኙ በእያንዳንዱ መንደሮችና ከተሞች ውስጥ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍለጎት የለውም” ብለዋል።
ነገር ግን ከዚህ በኋላ ህወሓት ምንም አይነት ጥቃት ለመፈጸም እንዳይችል ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ነገር መንግሥታቸው እንደሚያደርግ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል። ጨምረውም መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ያለውን መብት ተግባራዊ እንደሚያደርግና ትግራይን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የፈደራሉን ሠራዊት የማሰማራት መብቱን እንደሚያስከብር ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን የሚመረምር አካል ለማቋቋም ያሳለፈውን ውሳኔም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ይቋቋማል በተባለው አጣሪ ቡድን ላይ ከመጀመሪያው አንስቶ የነበራትን ተቃውሞ ያብራሩት አምባሳደር ሬድዋን ውሳኔው “ተቀባይነት የሌለውና ኢትዮጵያም ከቡድኑ ጋር አትተባበርም” ሲሉ የአገራቸውን ተቃውሞ በድጋሚ ገልጸዋል።
ትግራይን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ እርዳታ ሂደት ማባራሪያ የሰጡት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ቢሆንም የህወሓት እምቢተኝነትና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቡድኑን አፍራሽ ተግባር ለማውገዝ ያሳየው ግዴለሽነት የእርዳታ አቅርቦቱን አጓትቶታል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ሰኔ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ባወጀበት ጊዜ ህወሓት ተመሳሳይ እርምጃ ሳይወስድ ሲቀር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ ከዚያ በኋላ ተከትለው የመጡት ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።
ይህም ህወሓትን አደፋፍሮ አጎራባች ክልሎችን በመውረር በርካታ ጭፍጨፋዎችን በመፈጸሙ፣ መሠረተ ልማቶችን በማውደሙ፣ ሐይማኖታዊ ስፍራዎችን በመዳፈሩ እና ሴቶችን በቡድን እንዲደፍሩ በማድረጉ እርዳታ በሚያልፍባቸው መንገዶች ላይ ባሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል ብለዋል። ሚኒስትሩ ጨምረውም ከ1010 በላይ የእርዳታ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች በህወሓት ተጠልፈው ሲወሰዱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዝምታ መመልከቱን ጠቅሰው፣ ይህ ድርጊት በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስላለው በቀላሉ መታየት አልነበረበትም ሲሉ ወቅሰዋል።
ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ የቆየው ጦርነት፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚገመት ሲሆን በመቶ ሺዎች ለተፈናቃይነት እንዲሁም ከ9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ ለእርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል። ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቶ የነበረው እና አንድ ዓመት ያለፈው ጦርነት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ባካሄደው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የህወሓት ኃይሎችን ከአብዛኞቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ለማስወጣት ችሏል።
ህወሓት ግን በስልታዊ ውሳኔ ተዋጊዎቹን ከአንዳንድ ቦታዎች ማስወጣቱን ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደግሞ “ለሰላም ዕድል ለመስጠት” ኃይሎቹን ከአጎራባች ክልሎች ማስወጣቱን አሳውቆ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ውይይት እንዲጀመር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።
ምንጭ – ቢቢሲ