የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት ልዩ ስብሰባ በመጪው አርብ ለማካሄድ የያዘውን ውጥን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃወመ።

የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ስብሰባው እንዲደረግ ያቀረበው ጥያቄ ከምክር ቤቱ 47 አባላትና ታዛቢዎች መካከል በአንድ ሦስተኛው የተደገፈ ሲሆን ከእነዚህም መካካል ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትገኝበት ሮይተርስ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደች ባለበት ጊዜ ልዩ ስብሰባ መጥራት “ፖለቲካዊ ፍላጎት” አለው ስትል ተቃውማዋለች።

የተባባሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጋር በመሆን በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ መርመራ አካሂደው ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በአውሮፓ ሕብረት እና ታዛቢዎች ጥያቄ የሚካሄደው ስብሰባው በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህም ተቀባይነትን ካገኘ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ያደርጋል።

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በሰጠው ምላሽ፤ ጄኔቭ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አማካይነት እየተካሄደ ባለው ሁኔታ ግራ መጋባቱንና ማዘኑን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል የጋራ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱም ይፋ መደረጉን አስታውሶ፣ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ይህ ልዩ ስብሰባ የመንግሥትን ጥረት ከግምት ያላስጋባ ነው ብሏል።

ጨምሮም ይህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሊካሄድ የታቀደው ልዩ ስብሰባ አንዳች አይነት ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት አላማ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ ከዚህ ቀደምም በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ጫና ለማሳደረ ጥረት መደረጉን በማመለከት ተቃውሞታል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ አባላት ልዩ ስብሰባውን በመቃወም ድምጽ በመስጠት “ፖለቲካዊ አላማን ያነገበ” ውጤት ለማምጣት ያለመውን ስብሰባ ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቃለች።

አያይዞም ምክር ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በአፋርና በአማራ ክሎች ውስጥ በህወሓት ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጭፍጨፋዎችን በተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ነው በማለት ሐሳብ አቅርቧል። ከዚህ ቀደም በመንግሥታቱ ድርጀት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አማካይነት ለወራት በተደረገ ምርመራ በትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ዝርዝር ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጸሙት የመብት ጥሰቶች የጦር ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ አፋርና አማራ ክልሎችን ባዳረሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ሲገመት ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል እና ለእርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች የረድኤት ተቋማት ገልጸዋል።

በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በሚመለከትም በመንግሥታቱ ደርጅት የተካሄደው ምርመራና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ያወጧቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ