አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ላ73ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችንና ባህሪያችን ሊተገበር የሚገባው ቢሆንም ቀኑ በአለም አቀፍ ደረጃ መዘከሩ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር የአለም ህዝቦች ሁሉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በሰሜኑ የሀገራችን ነፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክኒያት የተላያዩ መጠነ ሰፊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ከኢትዮጲያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ምርመራ በማድረግ የደረሰውን ጉዳት መጠን እና አይነት በመለየት የመፍትሄ ኣቅጣጫዎች ማስቀመጣቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም እነዚህ አካላት ላደረጉት ጥረት ያለንን ከፍተኛ አድናቆት በድርጅታችን ስም እየገለጽን ወደፈትም እንዲህ አይነቱ ተግባር ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት በተለይም የህውሃት ሃይሎች ተቆጣጥረዋቸው በነበሩት የአማራ እና አፋር ክልሎች ኣሰቃቂ እና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የመንግስት እና የግል ንብረቶች እና መሰረተ ልማቶች ውድመት እና ዝርፊያ ተፈፅሟል፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም የወደሙ እና የተዘረፉትን መሰረተ ልማቶች በማደስ እና በማሟላት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

ነገር ግን ከእነዚህ መልሶ የማቋቋም ስራዎች ጎን ለጎን የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚገባ የማጣራት፣ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ እና ወንጀለኞችን ለፍትህ የማትረብ ስራዎች ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የሆኑ ዜጎች በተለይም ኣስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸው ሴቶች እና ህፃናት የሚያስፈልጋቸውን እገዛ እና ድጋፍ ማድረግ ከፍተኛ ትኩረትን እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እርብርብ ይሻል።

በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥን፣ መሰነድን እና ወንጀለኞችን ለፍትህ ማቅረብን ብሎም ተጎጂዎችን መርዳትን ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡትና በተግባር የተደገፉ እርምጃዎችንም በአፋጣኝ እንዲተገብሩ ድርጅታችን ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጲያ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ድርጅታችንም እንደ አንድ አገር በቀል የሰብአዊ መብት ድርጅት በጥሰቶቹ ዙሪያ ምርምር በማካሄድና መረጃዎችንም በማሰባሰብ ረገድ ያለበት የአቅም ውሱንነት እንደተጠበቀ ሆኖ የድርሻውን ሊወጣ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *