የተባበሩት መንግሥታት ባጸደቀው “የፓሪስ መርኆዎች” በተሰኘው መለኪያ መሰረት የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተአማኒነቱ ወደ ከፍተኛው ደረጃው ‘ኤ’ እንዲገባ ዓለም አቀፉ የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ጥምረት መወሰኑ ይፋ ተደረገ።
ጥምረቱ በመላው ዓለም ያሉ 118 ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማትን በአባልነት ያቀፈና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በፀሐፊነት የሚመራው ስብስብ ነው። የፓሪስ መርኆዎች እንደ ኢሰመኮ ያሉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ተቋማት ከሚሰሩባቸው ሕጎች፣ ከዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው፣ ከፖሊስ፣ ከአባልነት እንዲሁም በሚያንቀሳቅሱት ንብረት ላይ ካላቸው የማስተዳደር ሥልጣን በመነሳት ገለልተኛና ራሳቸውን ችለው የቆሙ መሆናቸውን የሚመዝን ሰነድ ነው።
በዚህም መሰረት ኢሰመኮ ለጥምረቱ የእውቅና ንዑስ ኮሚቴ ባለፈው ጥቅምት ወር ባቀረበው የጥያቄ ማመልከቻ መሠረት አዲሱ ደረጃ እንደተሰጠው የመብት ተቋሙ ጠቅሷል። “ጥምረቱ ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን ለመከላከል እና ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ጥረት ብሎም ከስምንት ዓመታት በፊት በነበረው ግምገማ ወቅት ይሻሻሉ የተባሉ ነጥቦችን በማሻሻሉን እንደሚያበረታታ ገልጿል” ሲል በመግለጫው አመልክቷል።
በፓሪስ መርኆዎች መሰረትም አንድ ተቋም ባለው ሥልጣን እና ሥልጣኑን የሚተገብርበት አቅም፣ አካታችነት፣ ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፣ ብሎም ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር ያለው ሥራ ግንኙነት ተጨማሪ መለኪያዎች ናቸው። ኢሰመኮ እንደገለጸውም ለአዲሱ የደረጃ ‘ኤ’ ማሻሻያው ዋነኛ ምክንያቶች ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ እንደአዲስ መርቀቁ ይገንበታል። ይህም ተቋሙ ያለውን የፋይናንስ ብሎም የሥራ ነጻነት በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና መጫወቱም ተገልጿል። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የመከታተል ብሎም የማረሚያ እና ማቆያ ቦታዎችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመጎብኘት ነጻነትን የሰጠ አዋጅ መሆኑንም ኮሚሽኑ አክሏል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ለተቋሙ የማሻሻያ ሥራዎች ብሎም የኮሚሽኑን ኃላፊነት ለመተግበር ባልደረቦቻቸው “አስቸጋሪ” ባሉት ሁኔታ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። “የኮሚሽኑ ደረጃ ወደ ከደረጃ ‘ቢ’ ወደ ‘ኤ’ ከፍ ማለቱ ተቋሙ እንደ አንድ ገለልተኛ እና ውጤታማ የሰብአዊ መብት ተቋም ከዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላቱን የሚያረጋግጥ ምስክር ነው” ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የኢሰመኮ ለቢቢሲ በላከው መግለጫም ይህ እንዲሳካ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል። ኢሰመኮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ክትትል በማድረግ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል። በቅርቡም በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ከመንግሥታቱ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ጋር በመተባበር ምርመራ አድርጎ ሪፖርቱ በቅርቡ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።
ምንጭ – ቢቢሲ