በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውና አንድ ዓመት የተሻገረው ጦርነት በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስተናገደ ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለይ የጦርነቱ ሂደት ባልተጠበቁ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተሞላ በመሆኑ ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለመተንበይ ለበርካቶች አስቸግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ መሪነት ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ ቁልፍ ሚና የነበረው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ ቢሄድም፤ ወደ እንዲህ አይነቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ይገባል ብለው የጠረጠሩ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቀያየሩ ወታደራዊ ኃይልን የሚያሳዩ ትርኢቶች፣ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የምርጫ መራዘም፣ በትግራይ የተናጠል ምርጫ መካሄድና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጥ ከዕለት ዕለት ውጥረቱን አባብሶ ወደ መጨረሻው ደረጃ አድርሶታል።
በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት በህወሓት የሚመራውን የክልሉን አስተዳደር ለማስወገድ ጊዜ የሚፈለግና የተራዘመ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ቢገምቱም፣ ከሦስት ሳምንታት በላይ የቀየ አልነበረም። የፌደራሉ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ የበላይነትን አግኝቶ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ቢቋቋምም ክልሉ ሳይረጋጋ አማጺያኑ የሚፈጽሙት የሽምቅ ጥቃትና ውጊያ ለወራት ቀጥሎ በሰኔ ወር ላይ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል።
የህወሓት ማንሰራራት
የትግራይ ክልልን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ መልሶ የተቆጣጠረው ህወሓት፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ አንሰራርቶ ተዋጊዎቹን ተዋሳኝ ወደሆኑት የአፋርና የአማራ አካባቢዎች በማሰማራቱ ጦርነቱ ወደ ሌሎች ቦታዎች ተስፋፍቶ ለወራት ቆይቷል። በዚህም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን በመቆጣጠር ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በህወሓት ኃይሎች መፈጸማቸውን ክልሎቹና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት አድርገዋል።
ጦርነቱ አንድ ጊዜ ጋብ ሌላ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሎ በተለይ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በተጠናከረ ሁኔታ ተካሂዶ፣ አማጺያኑ በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት የሰሜንና የደቡብ ወሎ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን ለመያዝ ችለው ነበር። በተለይ የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች እጅ ሥር ከወደቁ በኋላ፣ መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ጋር በመሆን ወደ መሃል አገር የሚያደርጉትን ዘመቻ ሲያጠናክሩ፣ በአፋር በኩል ደግሞ ጭፍራ የተባለችውን ቁልፍ ከተማ ይዞ አዲስ አበባን ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል።
ጦርነቱ ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ ከዚያም ወደ ሰሜን ሸዋ እየተስፋፋ ሲመጣ የአማራና የአፋር ክልሎች ከልዩ ኃይሎቻቸው በተጨማሪ ነዋሪዎቻቸው ከአማጺያኑ ጋር በሚደረገው ፍልሚያ እንዲሳተፉ፣ የፌደራል መንግሥቱ ደግሞ ሁሉም ዜጋ ለዘመቻው የሚችለውን ሁሉ እንዲያደረግ ጥሪ አቀረቡ። አማጺያኑ በበኩላቸው በአገሪቱ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ካሏቸው ሌሎች ቡድኖች ጋር በአሜሪካ ስምምነት በማድረግ፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ አዲስ አበባ ከመግባት የሚያስቆማቸው ኃይል እንደሌለ፣ ጦርነቱም በእነርሱ የበላይነት እንደሚያበቃ በመግለጽ ቀጣይ ዕቅዳችን ያሉትን ሲገልጹ ተደምጠዋል።
የሰላም ጥረት
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የአፍሪካ ሕብረትና የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕከተኞች ጦርነቱ በድርድር እንዲያበቃ አዲስ አበባና መቀለ በመሄድ ጥረት ያደርጉ ነበር። ነገር ግን በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይሰማ ኦባሳንጆና ፌልትማን ወደ መጡበት ሲመለሱ ጦርነቱ በነበረበት ቀጥለ። መንግሥት ከመነሻው በአሸባሪነት ከሰየመው ህወሓት ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ ቢያሳውቅም፣ በርካቶች በአማራ እና በአፋር ክልሎች የደረሰውን ውድመትና መፈናቀል በመመልከት ድርድር ሊኖር ይችላል ብለው ገምተው የነበረ ቢሆንም ምንም ለውጥ ሳይታይ እስካሁን ዘልቋል።
በአማጺያኑ በኩል የቀረቡት የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች በመንግሥት በኩል ቦታ ካለማግኘታቸውም ባሻገር፣ በርካታ አካባቢዎችን እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚዘልቀውን መንገድ በመያዝ ሰሜን ሸዋ ሲቃረቡ ፍጥጫውን በጦርነት ለመፈጸም ቆርጠው ነበር። በተለይ ቁልፍ የሆኑት የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞች መያዝ የህወሓት ኃይሎች ተጠናክረው የበለጠ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ መግፋት እንደሚችሉ በማመናቸው የድርድር ጉዳይ እንዳበቃለት በይፋ ወጥተው መናገር ጀምረው ነበር።
የትግራይ ኃይሎች አዛዥ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄነራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይም ተዋጊዎቻቸው ደሴን ይዘው ወደ ሸዋ ሮቢት ባቀኑበት ጊዜ ጦርነቱ እንዳበቃና ለድርድር የሚበቃ አስተዳደር እንደሌለ በመናገር የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በሂደት ላይ እንደሆኑ ገልጸው ነበር።

ሽሽት ከአዲስ አበባ
የአማጺያኑ ወደፊት መግፋትን ተከትሎ በተለይም የደሴ በአማጺያኑ መያዝና ጦርነቱ ወደ ሰሜን ሸዋ መስፋፋቱ ከባድ ስጋት የፈጠረ ሲሆን መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ። ምዕራባውያን አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ጦርነቱ አዲስ አበባ ሊደርስ ይችላል ብለው በመስጋት ዜጎቻቸውና ሠራተኞቻቸው በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ በይፋ አስጠንቅቀዋል። አንዳንዶችም ከአገሪቱ መውጣት ለሚፈልጉ የገንዘብ ብድርን ጨምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
መንግሥት ግን እነዚህ ማሳሰቢያዎች ሆን ተብሎ ጫና ለመፍጠር የተደረገ እንጂ፣ በተለይ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለዚህ የሚያደርስ የፀጥታ ስጋት የለም በማለት ተቃውሞውን ገልጿል። ቢሆንም ግን ዲፕሎማቶችና የፖለቲካ ተንታኞች ተኩስ አቁምና ድርድር ተደርጎ ከስምምነት እስካልተደረሰ አማጺያኑ ወደ አዲስ አበባ የመግባታቸውና ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ አሸንፎ መስከረም ወር ላይ የተመሰረተው መንግሥት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አደጋ ውስጥ ሊወቅድ እንደሚችል ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የኦሉሴጉን ኦባ ሳንጆ እና የጄፍሪ ፌልትማን ጥረትም መንግሥትና አማጺያኑን በማቀራረብ በሕዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ሁለተኛዋን አገርና የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል የሆነችውን ኢትዮጵያን ከከፋ ቀውስ ለመታደግ ያደረጉት ጥረት ውጤት ማስገኘት አልቻለም። ኦባሳንጆ ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም የተስፋ ጭላንጭል እንዳለ ለተባባሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ገልጸው አዲስ አበባና መቀለ ቢመላለሱም እስካሁን ድረስ ያገኙት ምላሽ አልታወቀም። የኃያሏ አገር ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ፌልትማንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከአማጺያኑ ተወካዮች ጋር ቢነጋገሩም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያገኙ ወደ ዋሽንግተን ተመልሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ
ጦርነቱ በሰሜን ሸዋ የተለያዩ አከባቢዎች ተስፋፍቶ በቀናት ውስጥ ምን ሊከሰት እንደሚችል ባልታወቀበት ጊዜ ነበር የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔ ማሳለፉ የተነገረው። ፓርቲው በምን ጉዳይ ላይ እንደተወያየ እና ያሳለፈው ውሳኔ በዝርዝር ሳይገለጽ ከስብሰባው ማብቃት ከሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትኛውም ወገን ያልጠበቀውን ውሳኔ ይፋ አደረጉ። ይህም በበርካቶች ዘንድ ግራ መጋባትና ምን ሊፈጠር ይችላል የሚል ጥያቄን አጭሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነታቸው ከዋና ከተማዋ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሱትን አማጺያንን ለመመከት ሠራዊታቸውን በመምራት ወደጦር ግንባር ለመሄድ መወሰናቸው የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ከዚህ ይልቅ ለድርድር በር መክፈት የተሻለ ይሆናል በማለት ውሳኔውን የተቹም ነበሩ። ጦርነቱ ገፍቶ ሰሜን ሸዋ መድረሱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩን ለመምራት ወደ ጦር ግንባር ማምራታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ከማጉላቱ ባሻገር፣ ጦርነቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።
ፌልትማን ዋሽንግተን ከተመለሱ በኋላ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህወሓትን ከአማራና የአፋር ክልሎች አስወጥቶ ወደ ትግራይ እንዲመለስ ማድረግ እንደሚቻል እንደሚያምኑ እንደገለጹላቸው አንስተው ነበር። ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረውን የጦርነት ሂደት በማሰብ ፌልትማን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳዩት የራስ መተማመን ላይ ጥያቄ ውስጥ በማስገባት “የኢትዮጵያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ የተፈጠረውን ሁሉ በካርታ ላይ በማየት ብቻ ይህ ሊሆን እንደማይችል እርግጠኛ መሆን ይቻላል” ብለው ነበር። በዚህም ሳቢያ በጦርነቱ ከመግፋት ይልቅ መንግሥት ከህወሓት ኃይሎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ለጦርነቱ መፍትሔ እንዲገኝ እንዳበረታቱ ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ግንባር መገኘት
በርካቶችን ግራ ያጋባው የጠቅላይ ሚኒስተሩ ውሳኔ ምን ይዞ ሊመጣ እንሚችል እርግጠኛ ያልሆኑ ሰዎች የተለያዩ መላምቶች ከማስቀመጣቸው ባሻገር ጦርነቱ የበለጠ ደም አፋሳሽና የተራዘመ ሊሆን እንደሚችል ሲገልጹ ቆይተዋል። ነገር ግን ከሳምንት በኋላ እየተሰማ የመጣው ዜና የጦርነቱ የኃይል ሚዛን መቀየሩን የሚያመላክቱ ነበሩ። በቀዳሚነት በአፋር በኩል በተደረጉ ከባድ ውጊያዎች ከጂቡቲ ወደሚመጣው መንገድ ለመቅናት ወሳኝ የሆነው ጭፍራ በመከላከያ ሠራዊቱና በአፋር ኃይሎች ከአማጺያኑ ነጻ መውጣቱ ተነገረ።
በተከታይም ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ያሉ ቦታዎች ከአማጺያኑ እጅ ወጡ፣ ስልታዊ ቁልፍ ቦታ የሆነችው ጋሸናም ከከባድ ውጊያ በኋላ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቷ ሲነገር፣ ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማም በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ዋለች። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምና ጉልህ ሚና ሲጠቀስ ቆይቷል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱት ጦርነቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች በጣምራ መሳተፋቸው የተነገረ ሲሆን ዘመቻውም በተከታታይ የተደረገ ነው።
ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በአማጺያኑ እጅ ሲገቡ በጦርነቱ ሂደት ላይ ጉልህ ለውጥ እንዳመጣው ሁሉ፣ እነዚህ ከተሞች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ተመልሰው መግባታቸው የጦርነቱ አቅጣጫ መቀየርን አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ። በህወሓት በኩል ከሰሜን ሸዋ አስከ ደሴ እንዲሁም በአፋር ክልል ውስጥ ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው በደረሰባቸው ሽንፈት ሳይሆን በስልታዊ ውሳኔ ለቅቀው የወጡባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
በቀጣይስ ወዴት?
አስካሁን በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ከተነገሩት አካባቢዎች አንጻር በአፋር፣ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም በሰሜንና ደቡብ ወሎ ውስጥ የሚገኙ በአማጺያኑ ተይዘው የነበሩ አብዛኞቹ ቦታዎች ነጻ እንደሆኑ ይነገራል። ዘመቻው ቀጥሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል ያሉ የቀሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ ከቻለ ቀጣይ የጦርነቱ አቅጣጫ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አስከ አሁን ድረስ የታወቀ ነገር የለም።
ሠራዊቱ እንደዚህ ቀደሙ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ ይገባ ይሆን ወይስ ፌልትማን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገሩኝ እንዳሉት አማጺያኑን ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ከወጡ በኋላ ሌላ አማራጭ ይፈልጉ ይሆን? ባለፈው ሳምንት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጄነራል ባጫ ደበሌ ለዚህ ጥያቄ የሰጡት መልስ “እኛ እዚህ ጋር እንቆማለን አንልም። ወታደራዊ ሁኔታው ነው የሚወስነው። ጦርነት በእርግጠኝነት የሚነገር ነገር አይደለም። አንሰርቴይኒቲ (የማይገመቱ ነገሮች) የሞላበት ነው። ስለዚህ በቀጣይ የሚፈጠረው ነገር ነው የሚወስነው። ነገር ግን እኛ አንቆምም” የሚል ነበር።