ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት እና ፈንታሌ ወረዳዎችን በሚያዋስን እና ካራ ወይም ሞቶማ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ 14 ሰዎች ተገድለው ነበር።

ከሟቾቹ መካከል አንዱ ደግሞ የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩ ይገኙበታል። የክልሉ መንግሥት አባ ገዳ ከድር ሃዋስን የገደለው “ሸኔ” ነው በማለት በሽብርተኛ ቡድንነት የተሰየመውን ታጣቂ ቡድንን ይከሳል። ቢቢሲ ያነጋገረው የሟች ቤተሰብ እና የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው አባ ገዳውን ጨምሮ ረቡዕ ዕለት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 14 መሆናቸውንና የተገደሉትም በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ነው ይላሉ። እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ በበኩሉ አባ ገዳውን ጨምሮ በመንግሥት ኃይል የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 23 ናቸው ይላል።

ስለ ግድያ የምናውቀው

ግድያው የተፈጸመው የከረዩ ኦሮሞዎች የገዳ ሥነ ሥርዓት የሚያከናውኑበት፤ የገዳ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ሰፍረው በሚገኙበት ቦታ መሆኑን በጥቃቱ ወንድሙ የተገደለበት የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ ይናገራል።

ረቡዕ ኅዳር 22/2014 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች አባ ገዳዎቹ ተሰብስበው የሚገኙበት ቦታን ከበው ከያዙ በኋላ፤ 41 ሰዎችን ይዘው ሄዱ ይላል። ይህ ወንድሙ የተገደለባት የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ እንደሚለው በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከሄዱት መካከል አስከሬናቸው ከተገኘ 14 ሰዎች እንዲሁም ከጥቃቱ ማምለጥ ከቻሉ ሁለት ሰዎች ወጪ የተቀሩት ሰዎች የደረሱበት እንደማይታወቅ ለቢቢሲ ተናግሯል። የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በበኩሉ አርብ ዕለት ባወጣት መግለጫ የከረዩ አባ ገዳ የተገደሉት “በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ነው” ብሏል። የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ከአባ ገዳው በተጨማሪ ሰዎች ስለመገደላቸው ያለው ነገር የለም።

“የከረዩ ሕዝብ . . . የድጋፍ ሰልፍ መውጣቱን የተከታተለው ሸኔ፤ ‘ሕዝብ ያነሳሳህብን አንተ ነህ’ በማለት የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስን አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ገድሏል” ብሏል የክልሉ መንግሥት ያወጣው መግለጫ። መንግሥት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውን ቡድን ‘ሸኔ’ በማለት የሚጠራው ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወራት በፊት ህወሓትን ጨምሮ ይህንን ቡድን አሸባሪ ሲል መፈረጁ ይታወሳል። የኦሮሞ ነጻነት ጦር በበኩሉ ግድያውን በተመለከተ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ “የከረዩ ንጹሃን ዜጎች በመንግሥት ኃይሎች መገደላቸው አስደንጋጭ ነው” ብሎታል። “የመንግሥት ኃይሎች እና ብልጽግና ፓርቲ ሰላማዊ ሰዎችን ዝም ለማሰኘት አቅደው የፈጸሙት ግድያ ነው” ብሏል የኦሮሞ ነጻነት ጦር በመግለጫው።

ረቡዕ ዕኩለ ቀን ላይ ፀጥታ ኃይሎች አባ ገዳዎቹ ተሰብስበው የነበሩበትን ቦታ ከከበቡ በኋላ 41 ወንድ ሰዎችን ለይተው ድበደባ እንደፈጸሙባቸው ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የሟች ወንድም ይናገራል። እንደ ነዋሪው ከሆነ የመንግሥት ኃይሎች 41 ሰዎችን ሜጢ ተብሎ ወደሚጠራ ስፍራ ይዘዋቸው ከሄዱ በኋላ ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች ማምለጣቸውን ይናገራሉ። አመለጡ ከተባሉት ሁለት ሰዎች፤ የ14 ሰዎችን ግድያ መስማቱን እና ከሌሎች ጋር በመሆን የ14 ሰዎች አስክሬን ስለማንሳቱም ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል። ቢቢሲ ያነጋገራው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ 40 ሰዎች ከተወሰዱ በኋላ አባ ገዳ ከድር ሃዋስን ጨምሮ ረቡዕ ምሽት ላይ 14 ሰዎች መገደላቸውን ይናገራል። ይህ ነዋሪ የአባ ገዳ ከድር ሃዋስ ሥርዓተ ቀብር ቦሰት ወረዳ ቃዋ ተብሎ በሚጠራ መንደር መፈጸሙን ተናግሯል።

የተገደሉት ሰዎች ስርዓተ ቀብር አርብ ሕዳር 24 ተፈጽሟል።

ረቡዕ እኩለ ቀን ላይ ተይዘው የተወሰዱት ሰዎች ረቡዕ ምሽት ከተገደሉ በኋላ አስክሬናቸውን ከወደቀበት ሳይነሳ እስከ ሐሙስ ምሽት መቆየቱን ሁለቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ። የሰዎቹ ሥርዓተ ቀብርም አርብ ዕለት መፈጸሙን ይናገራል። ሁለቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት 41 ሰዎች ከነበሩበት ቦታ ተይዘው የሄዱት የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ ደንብ በለበሱ ግለሰቦች ነው።

‘ከግድያው በፊት ግጭት ተከስቶ ነበር’

14ቱ ሰዎች ከመገደላቸው አንድ ሳምንት በፊት የፀጥታ ኃይሎች ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች ጋር ሲዋጉ ነበር፣ ይላል ይህ ወንድሙ የተገደለበት ነዋሪ። ከአንድ ሳምንት በፊት ፈንታሌ ወረዳ ከአፋር እና አማራ ክልል በምትዋሰንበት ቦታ ላይ በነበረ የተኩስ ልውውጥ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ከባድ ጉዳት ስለመድሱ ሰምቻለሁ በማለት ያስረዳል። በሰዎቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ከዚህ ጋር ሳይገናኝ አይቀርም በማለት ወንድሙን ያጣው ነዋሪ ግምቱን ይሰጣል። ይሁን እንጂ ይህ ነዋሪ፤ “አባ ገዳዎች ግጭት ሲከሰት ያስታርቃሉ እንጂ በጦርነት ተሳታፊ አይሆኑም” ይላል።

ምንጭ – ቢቢሲ