በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የቆዩትን የአማራና የአፋር አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ዘመቻ የጀመረው የመከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱን መንግሥት አስታወቀ።
ቅዳሜ ማምሻውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት የተለያዩ ከተሞችን የተለያዩ ከተሞችን ከህወሐት በማስለቀቅ መቆጣጠሩን ገልጿል። “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” ተብሎ በተጠራው ዘመቻ የመከላከያና የክልል ጥምር ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በተለያዩ ግንባሮች በርካታ ከተሞችን ለመቆጣጠር እንደቻሉ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት በጋሸና ግንባር ቀውዝባ፣ ጭላ ከተሞችና አካባቢያቸው፤ በወረኢሉ ግንባር አጅባር፣ ተንታ እና ዶባ ከተሞችና አካባቢያቸው እንዲሁም በከሚሴ ግንባር ማጀቴ፣ ጭረቲ፣ ከሚሴ፣ ርቄ፣ ወለዲ፣ አልቡኮ ከተሞችን እና የቃሉ ወረዳ አብዛኛው ክፍልን ሠራዊቱ ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጿል። ጥምር ኃይሉ እነዚህን አካባቢዎች ከህወሓት ኃይሎች በማስለቀቅ ከተቆጣጠረ በኋላ የደቡብ ወሎ ዋና ከተማ ከሆነችው ደሴ በቅርብ ርቀት ወደምትገኛውና የኢንዱስትሪ መናኸሪያ ወደ ሆነችው ኮምቦልቻ እያመራ መሆኑን መግለጫው አመለክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ ሠራዊቱን ለመምራት ወደ ጦር ግንባር ከሄዱ ከቀናት በኋላ በተካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተዘግቧል። ከእነዚህም መካከል ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማን ጨምሮ ቁልፍ ወታደራዊ ጠቀሜታ አላቸው የሚባሉትን በአፋር ክልል ጭፍራን በአማራ ክልል ደግሞ ጋሸናን ነጻ ለመውጣት መቻሉ ተገልጿል።
በህወሓት በኩል እንደተነገረው ከተባሉት አካባቢዎች ኃይሎቹ እንዲወጡ የተደረገው በስልታዊ ውሳኔ መሆኑን ቢገልጽም፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “አማጺው ሽንፈት ገጥሞት ነው” ብለዋል። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ሰኔ ወር ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ቆይተው ነበር። የደቡብ ወሎ ቁልፍ ከተሞች ደሴና ኮምቦልቻ በአማጺው መያዛቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውጊያዎች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይነገራል።
ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው እየተካሄዱ ነው።
ምንጭ – ቢቢሲ