ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከህወሓት አማጺያን ነጻ ወጥታ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥሩ ስር መግባቷን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

ለወራት በህወሐት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆየችው ላሊበላ ረቡዕ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በሚሊሻና በፋኖ በተካሄደ ዘመቻ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባቷ ተገልጿል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን እንዳስታወቀው የመንግሥት ጥምር ኃይሎች ታሪካዊቷን የላስታ ላሊበላ ከተማንና የላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ተቆጣጥረዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው የላሊበላ ከተማ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ነበር በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋለችው።

ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ለአራት ወራት ያህል የቆየችው የላሊበላ ከተማ እና አካባቢዋ በዛሬው ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ነጻ መውጣቷን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትም በማኅበራዊ ገጹ ላይ አስፍሯል። ህወሓት በበኩሉ ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ የተወሰኑ አካባቢዎች “ለስትራቴጂ ሲል መውጣቱን” ገልጿል። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር 310 ኪሎ ሜትሮች እንዲሁም የህወሓት አማጺያን መቀመጫ ከሆነችው መቀለ በስተደቡብ 348 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት።

ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው የላሊበላ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ትልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶችን የምታስተናግድ ከተማ ናት። በትናንትናው ዕለት ረቡዕ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ቃለ አቀባዩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጦሩ በስትራቴጂ ቁልፍ የምትባለውን ደሴን “በአጭር ጊዜ ውስጥ” መልሶ እንደሚቆጣጠር እርግጠኛ መሆኑን መናገራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠሩን ያስታወቀው መንግሥት ከአዲስ አበባ 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠሩን አስታውቋል። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወታደራዊ መለዮ ለብሰው አካባቢያቸውን ሲቃኙ የሚያሳይ ቪዲዮ ከሰሞኑ አሳይቷል። “ጠላት ተሸንፏል። የኛ ቀሪ ሥራ ጠላትን ተከታትሎ መደምሰስ ነው” ሲሉ በዛፍ ስር ለተቀመጡት ወታደሮች ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት የህወሓት መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሱት ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ ፅፈዋል።

ኢትዮጵያ ድሮኖችና የጦር መሳሪያዎች ከኢራን፣ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መቀበሏን ዶክተር ደብረ ጽዮን ተናግረዋል። ይህንን አስመልክቶ ከመንግሥት የተሰጠ ምላሽ የለም። የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በዚህ ሳምነት ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በጦር ሜዳ ላይ ባሉበት ወቅት የእለት ከእለት የመንግሥት ሥራ ኃላፊ ሆነው ከተሾሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተዋል። በኢትዮጵያ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት የሰብአዊ መብት ረገጣ ሪፖርቶችን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከአሜሪካ እና ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ጫና በሚደርስበት ወቅት ቻይና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የውጭ “ጣልቃ ገብነት” በማለት ስትቃወም ትሰማለች።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሰኔ ወር ላይ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል። የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው እየገለጹ ቆይተዋል። የደቡብ ወሎ ቁልፍ ከተሞች ደሴና ኮምቦልቻ በአማጺ መያዛቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይነገራል።

ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው ሲካሄዱ ቆይተዋል። በዚህም ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአፋርና በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙና በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩ ቁልፍ ከተሞችን የመንግሥት ኃይሎች አስለቅቀው መቆጣጠራቸው ተነግሯል። ዛሬ ጠዋት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በጋሸና፣ በወረኢሉ እና በሸዋ ግንባሮች በኩል በህወሓት ቁጥጥር ስር ነበሩ በርካታ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸውን አሳውቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ