የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ግዙፉ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ትዊተር ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾችን እያፈነ ነው አሉ።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት በሰጡት መግለጫ “ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾች እየታፈኑ ነው” ያሉ ሲሆን በአንጻሩ፤ ህወሓትን የሚደግፉና የመንግሥት ለውጥ እንዲካሄድ የሚቀሰቅሱ ሃሳቦች እንዲጸባረቁ ይፈቀዳሉ ብለዋል። ቢልለኔ በትዊተር ውስጥ የህወሓት ደጋፊዎች ስለመግባታቸው ለተቋሙ የፖሊሲ ቡድን ማሳወቃቸውንም ጨምረው ተናግረዋል። “በህወሓት እና በህወሓት ደጋፊዎች ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሐሰተኛ ዜናዎች መሰራጨታቸውን ቀጥለዋል” ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ የህወሓት አባለት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመጣል በይፋ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።
ቢልለኔ “እነዚሁ ግለሰቦች ከቀድሞ እና ከአሁን ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ የሚያሳይ ሾልኮ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ታይቷል” ሲሉ ሰሞኑን መነጋገሪያ የነበረውን ቪዲዮ ጠቅሰዋል። ትዊተር ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ማለቱ ይታወሳል። ግዙፉ ማኅበራዊ ሚዲያ ግጭት ቀስቃሽ እና ሰዎችን ዝቅ የሚያደርጉ ይዘቶችን እንደማያስተናግድ ገልጾ ነበር። ትዊተር ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የበርካቶችን ትኩረት ያገኙ ርዕሶችን ወይም ‘ትሬንዶች’ ማሳየት አቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ግንባር
ቢልለኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጦር ሜዳ ሄደው ጦሩን መምራት ከጀመሩ አንድ ሳምንት መሆኑን አስታውሰው፤ “የጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ጦር ግንባር መሄድን ምዕራባውያን በተሳሳት መንገድ ተረድተውታብል” ብለዋል። ቢልለኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር የሄዱት ጦርነቱ ተባብሶ በመቀጠሉ ሳይሆን፤ “ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ለመውጣት ነው” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መደበኛ ሥራቸው መቼ ይመለሳሉ ተበሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ በዚህ ቀን ብሎ መናገር አልችልም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር መገኘት የሠራዊት አባላት ሞራልን ከፍ ማድረጉ እና በዜጎች ዘንድ አንድነት መፍጠር ማስቻሉን ጠቅሰዋል። ፕሬስ ሴክሬታሪዋ በመግለጫቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህወሓት ተዋጊዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረባቸውንም አስታወሰዋል። ማክሰኞ ኅዳር 21/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦራቸው በተለያዩ ግንባሮች ድልን እየተቀዳጀ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከህወሓት ጎን የተሰለፉ ተዋጊዎች እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። ቢልለኔ በዛሬው መግለጫው፤ “ህወሓት የኢትዮጵያ ሰላም እና ደህንነት አደጋ አለመሆኑ እስከሚረጋገጥ ድረስ በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የሚወደሰው እርምጃ ይቀጥላል” ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ቢልለኔ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ሦስት ሳምንታት እንዳሳቆጠረ አስታውሰው፤ አዋጁ የሚፈለገውን ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁ በአገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር በማስፈለጉ እንደሆነ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጣም ውጤታማ ነው” ያሉት ቢልለኔ፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱ ፍተሻዎች ጦር መሳሪያዎች፣ ወታደራዊ መሳሪያዎች፣ የደንብ ልብሶች፣ የተለያዩ አገራት የደንብ ልብሶች፣ መገናኛ መሳሪያዎች እና ሐሰተኛ መታወቂያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ብሔራዊውን እና የክልል የአደጋ ስጋት እና መከላከል ኮሚሽን በመጥቀስ በአማራ እና አፋር እየተከናወኑ ስላሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች መረጃዎችን አጋርተዋል። ቢልለኔ በአማራ ክልል ጦርነቱን ተከትሎ 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀሉን እና 5.6 ሰዎች በግጭቱ ምክንያት መጎዳታቸውን ተናግረዋል። አብዛኛው ተፈናቃይ ከዋግ ኽምራ፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከማዕከላዊ ጎንደር፣ ከሰሜን ወሎ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ሸዋ እና ከወልቃይ ጸገዴ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአፋር ክልል ደግሞ በግጭቱ ተጎጂ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ260ሺህ በላይ መሆኑን አመልክተው ከ100ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል። የፌደራሉ መንግሥት ከክልል እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቢልለኔ በትግራይ ደግሞ ከአምስት ሳምንታት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ በረራ ወደ መቀለ ማደረግ መጀመሩን አስታውሰው፤ ጥሬ ገንዘብ እና እህል የጫሉ ከባድ ተሸከርካሪዎች በሰመራ በኩል ወደ ትግራይ እያቀኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራው ሪፖርታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ቢልለኔ አስታውሰዋል። በዚህ ሪፖርት ላይ በተቀመጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት ጠቅላይ ሚንስትሩ ተፈጽመዋል የተባሉ ጉዳቶችን ለማጣራት እና ለተጎጂዎች አስፈላጊውን ለማድረግ ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን ተናግረዋል።
ይህ ግብረ ኃይል አራት ኮሚቴዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፣ የመጀመሪያው ምርመራዎች እና ክስ መመስረት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ሁለተኛው ኮሚቴ ደግሞ ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን ይመለከታል። ሦስተኛው ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ሲመረምር፣ የመጨረሻው ኮሚቴ ደግሞ የሃብት እቅርቦት ላይ ይሰራል ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ መግለጫቸው።