በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ከሁለት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያየ ውድመት መድረሱን መንግሥት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒንስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ክልሎች በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አብራርተዋል። የህወሓት ኃይሎች በገቡባቸው በአምስት የአማራ ዞኖች ውስጥ በ1660 ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ውድመት መድረሱን ተናግረው ከእነዚህ መካከል 277 የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ በአፋር ክልል ደግሞ 455 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ብለዋል።
በአማራ ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት መካከል ሁለት የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ እንደወደሙም ተገልጿል። በትምህርት ቤቶች ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት በአማራ ክልል ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ሲስተጓጎሉ 47 ሺህ መምህር ደግሞ ከሥራቸው ተፈናቅለዋል። ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የወደሙ ትምህር ቤቶችን መልሶ ለመገንባታ ከአጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት በመንግሥት በኩል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የተጀመረው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ያደረሰ ሲሆን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሚሆኑ ሰዎችም የሰብአዊ እርዳታ ለመጠበቅ ተዳርገዋል። በጦርነቱ ሳቢያ ከትምህርት ተቋማት በተጨማሪ የጤና እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ውድመትና ዘረፋ የተፈጸመ ሲሆን እስካሁን የትኛውም ወገን ኃላፊነቱን አልወሰደም። በአሁኑ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ተጨማሪ ጉዳትና ውድመት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት አለ።
የሰብዓዊ እርዳታ
ሰላማዊት ካሳ በዛሬ መግለጫቸው ሌላው ያነሱት ጉዳይ በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ እየተከናወኑ ስላሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ነው። በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን ተሻግሯል ብለዋል። ለእነዚህ ተፈናቃዮችም መንግሥት 265 ሺህ ኩንታል ምግብ ማሰራጨቱን እና በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰው ማገዝ መቻሉን አብራርተዋል። በአፋር ክልል ደግሞ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 76 ሺህ ነው ያሉት ሚንስትር ድኤታዋ፤ ካለፈው ወር ወዲህ በአፋር ለተፈናቀሉ ሰዎች 36 ሺህ ኩንታል የእርዳታ እህል እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ወደ ትግራይ በዓለም ምግብ ድርጅት በኩል የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ባለፉት ቀናት በአየርና በሰመራ በኩል መቀጠሉን አመልክተው፤ በሰመራ በኩል አስፈላጊውን ሂደት ያለፉ 83 የእርዳታ እህል እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪኖች ወደ ወደ ክልሉ መላካቸውን አስረድተዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት አርብ አስታውቋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ቶመሰን ፊሪ ስዊትዘርላንድ ጄኔቭ ላይ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ ነው ብለዋል።