እሌኒ ገብረመድህን (ፒኤችዲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ካቋቋሙት ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባልነታቸው ከዛሬ ሕዳር 19 ዕለት ጀምሮ መነሳታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ዶ/ር እሌኒ ከገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪነታቸው የተነሱት በቅርቡ በዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል (ፒዲሲአይ) በተዘጋጀ የዙም ስብስባ ላይ “በሕጋዊ ምርጫ የተመረጠውን የኢፌዴሪ መንግሥት የመለወጥና የሽግግር መንግሥት የማቋቋም አጀንዳ ላይ በመሳተፍ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ በመታየታቸው” እንደሆነ ገልጿል። መግለጫው ዶ/ር እሌኒ በተካሄደው ድብቅ ስብሰባ ላይ ያነሷቸው ሃሳቦች ” በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀን ቡድን በግልጽ የሚደግፍ” ነው ብሏል።

በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰው የሰላም እና ልማት ዓለማቀፍ ማዕከል የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ማኅበር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ” የአገርን ሕልውናና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ድጋፍ ያደርጋል በሚል ” በሲቪል ማሕበረሰቦች ባለሥልጣን ፈቃዱ ተሰርዟል። የድርጅቱ ፍቃድ የተሰረዘው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማዕከላዊ ዕዝ መንግሥት አሸባሪ ብሎ ለፈረጀው ሕወሃት ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ ያመነውን ማንኛውም የሲቪል ማኅበራት ድርጅት ሕጋዊ ፍቃዱ እንዲሰርዝ በአዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መሆኑም ተገልጿል።

ከሰሞኑ በወጣው የዙም ስብሰባ ዶ/ር እሌኒ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስን ጨምሮ ሌሎች እውቅ ኢትዮጵያውያንና የቀድሞ የአሜሪካና የውጭ አገራት አምባሳደሮች ሲመክሩ የታዩ ሲሆን፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሯል። ይህንን ተከትሎ ዶ/ር እሌኒ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሁፍ፤ በስብሰባው ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ሆነ ተብሎ ከአውድ ውጭ እንደተወሰደባቸው ገልጸው፤ የስብሰባው ዓላማም በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋምን ጨምሮ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ የሚደረግ ማንኛውንም የመንግሥት ለውጥ ፈጽሞ እንደማይደግፉና የእርሳቸውም ተሳትፎ እንደ አንድ የኢትዮጵያን ሰላም የሚፈልግ ዜጋና በጦርነቱ ስለተጎዳው የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት መልሶ ግንባታ መፍትሄ ለመሻትና በግላቸው እንጂ ከቀጣሪ መሥሪያ ቤታቸው ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን የስራ ፈጣሪዎች የሚደግፈው ‘ብሉ ሙን’ የተሰኘ ድርጅታቸውም ለጊዜው ተዘግቶ መንግሥት ምርመራ እያደረገበት እንደሆነ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሳሙዔል በቀለ ከሰሞኑ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

አቶ ሳሙኤል የዶክተር ኢሌኒን ድርጊት ተቃውመው ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፍቃዳቸው ከሃላፊነት መልቀቃቸውንም በዚሁ ትዊተር መልዕክት አስፍረዋል። በሌላ በኩል ዶክተር ኢሌኒ ባለድርሻ የሆኑበት ምቹ የስራ ከባቢን ለመፍጠር በማቀድ ለአጭርና ለረጅም ጊዜ የስራ ቦታን የሚያቀርበው ‘ብሉ ስፔስ’ የተሰኘ ተቋም ባለድርሻዎች የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱና ያሲር ባግረሽ የዶክተር ኢሌኒን ተግባር እንደሚያወግዙ ከሰሞኑ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅም በድርጅታቸው አሳላጭነት የተዘጋጀው ውይይት የተሳሳተ ግንዛቤ በመፍጠሩ ይቅርታ ጠይቀው መግለጫ አውጥተዋል። ውይይቱ እንደተባለው ሚስጥራዊ እንዳልሆነና ከመንግሥት በኩልም በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተጋብዘው የነበረ ቢሆንም ስላልተመቻቸው አለመካፈላቸውንም አስረድተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የዛሬው መግለጫ በ2010 ዓ.ም የመጣውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በተደረጉ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በአገሪቷ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የልማት አቅጣጫዎች ገለልተኛ ምክር ለመስጠትና ግምገማ ለማድረግ እድል መሰጠቱን አስታውሷል። በዚህም መሠረት በ2013 ዓ.ም አስራ ስድስት አባላት ያሉት ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተሰይሟል። ከእነዚህ አማካሪዎች መካከል ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን አንዷ ነበሩ።

ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹ ያቋቋሙት ምክር ቤት ደንብ አባላቱ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ከየትኛውም ፓርቲም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነጻ መሆን እንደሚገባቸው መግለጫው አጣቅሷል። በመሆኑም ምክር ቤቱ ትናንት ኅዳር 18 ፣ 2014 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በምክር ቤት አባሏ ድርጊት ማዘኑን በመግለፅ ከገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዳይቀጥሉ መወሰኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።

ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን በሥራ ፈጠራቸው ወይም ለሥራ ፈጣሪዎች ዕድል በመስጠታቸው እንዲሁም የኢትዮጵያን የምርት ገበያን በማስጀመራቸው ይታወቃሉ። በቅርቡም በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ውስጥ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ ያለመውን አዲስ ዘርፍ በኃላፊነት እንዲመሩ መመረጣቸው የሚታወስ ነው።