እየተካሄደ ካለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ የተለያዩ ዘገባዎችና ትንታኔዎችን መስጠትና ማሰራጨት መከልከሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ።
ዕዙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ገምግሞ በሥራው ሂደት ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ናቸው ባለቸው አራት ጉዳዮች ላይ ሐሙስ ኅዳር 16/2014 ዓ.ም ባስተላለፈው ትዕዛዝ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችና መረጃዎች ከሚመለከተው አካል ውጪ መግለጽ እንደሌለበት አዟል። “ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ፣የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች በየትኛውም የመገናኛ አውታር መግለጫዎች መስጠትና ማሰራጨት” የተከለከለ መሆኑን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም “የሐሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም፣ የሽብር ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ በህልውና ዘመቻው ላይ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም” የአስቸኳይ ጊዜ ዕዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ዕዙ ከመረጃ ስርጭትና ከመገናኛ አውታሮች አሰራር ባሻገር ሌሎች ሁለት ትዕዛዞችን ያወጣ ሲሆን እነዚህም የሽግግር መንግሥት ስለመመስረትና የፀጥታ አካላት የደንብ ልብሶችን አጠቃቀም የሚመለከቱ ናቸው።
ዕዙ መንግሥትና ሕዝብ በአገሪቱ ህልውና ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቀልበስ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ “የሽግግር መንግሥት ወይም ሌላ ሕገ-ወጥ ቅርጽ ያለው መንግሥት እንመሠርታለን” በማለት እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ አዟል። በተጨማሪም የፀጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ የመከላከያ ሠራዊትን፤ የፌዴራል ፖሊስን፤ የክልል ልዩ ኃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስን የደንብ ልብሶች ለብሶ መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል።
እነዚህን አራት ትዕዛዛትን ተላልፈው በሚገኙ ተገኙት ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ዕዝ አስታውቋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በመዲናዋ አዲስ አበባ የሚገኙ አሰሪዎች ለሠራተኞቻቸው መደበኛ መታወቂያ ከመስጠት እንዲቆጡ የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አሳስቧል።
የቢሮው ኃላፊ ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ አዲስ መደበኛ መታወቂያ ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡ አንዳንድ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ስለማለታቸው ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ” ይህንንም አደጋ “በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ” ታስቦ እንደታወጀ መገለጹ ይታወሳል።
ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደንግጎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚከታተለውና የሚያስፈጽመው ‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ’ የተባለ አካል ሲሆን ይህ የተለያዩ አካላት የተካተቱበት ዕዝ በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
ምንጭ – ቢቢሲ