የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን አዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲው በኢትዮጵያ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ በተመለከተ የሚያወጧቸው መግለጫዎች ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞውን ሲገልጽ አዲስ አበባ ውስጥ በእንግሊዝና በአሜሪካ ኤምባሲዎች ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ።
ሐሙስ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙት የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ኤምባሲዎች ፊት ለፊት በመገኘት መንግሥታቱ ከወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ጉዳይ እየፈጸሙ ነው ያሉትን ጣልቃ ገብነት መቃወማቸው ተዘግቧል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ደግሞ ከአሜሪካ በኩል የሚወጡት ማስጠንቀቂያዎች የአገሪቱን ገጽታ ለማበላሸትና በዲፕሎማቶች ላይ ጫናን ለመፍጠር ያለሙ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል። ሚኒስትር ዲኤታው ለዚህ እንደማሳያ የጠቀሱት ከቀናት በፊት የአሜሪካ ኤምባሲና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ያወጣው በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚለውን ማስጠንቀቂያ ነው።
ማስጠንቀቂያው አሸባሪዎች በአገሪቱ ውስጥ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በመግለጽ የአሜሪካ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የሚገኙ “የዲፕሎማቲክ ተቋማትን፣ የቱሪስት ስፍራዎች፣ የትራንስፖርት ማዕከላትን፣ የገበያ ቦታዎች፣ በምዕራባዊያን ተቋማት፣ የመዝናኛ ቦታዎችና ሌሎችም ስፍራዎች” የሽብር ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ስለሚችሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የወጣው ማሳሰቢያ ተቀባይነት የሌለውና የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለማበላሸትና ጫናን ለመፍጠር የተደረገ ነው ሲሉ አጥብቀው ተችተውታል።
“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአዲስ አበባ ውስጥ ሰላም የለም፤ ለሽብር የተጋለጡ ናቸው በማለት ባለሐብቶችና ቱሪስቶች ከመምጣት እንዲቆጠቡ ለማድረግ የታለመ ነው።” ብለዋል። ሚኒስትር ዲኤታው ጨምረውም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ሽብርን በመከላከል አብራ ስትሰራ እንደቆየች ጠቅሰው፣ እንዲህ አይነት ስጋት በሚኖር ጊዜ መንግሥትና ኤምባሲው መረጃ በመለዋወጥ አስፈላጊው ዝግጅትና ጥንቃቄ ይደረግ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ከአሜሪካ በኩል የወጣው የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ግን ምንም ማስረጃ ሳይኖር በተናጠል ጥቃት እንደሚፈጸም በመግለጽ፣ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሕጎችና ልማዶችን የጣሰ ድርጊት መሆኑን ጠቅሰው ግንኙነትን የሚያበላሽ ነው ብለውታል።
በዚህም ምክንያት የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን የአዲስ አበባው የሚገኘው ኤምባሲው “ከእንደዚህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ እንዲቆጠብ” ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ለአሸባሪ ቡድን ድጋፍ መስጠት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው “በተለያዩ መንገዶች አሸባሪን ሲደግፉ ቆይቶ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም ይችላሉ ብሎ መግለጫ ማውጣት የማይመስልና የኢትየጵያን ሉአላዊነትን የሚጎዳ” ተግባር ነው በማለት ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ሚኒስትር ዲኤታው ጨምረው አንዳንድ ግለሰቦችና የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች የተለያዩ ጫናዎችን በዲፕሎማቶች ላይ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በተለይ በአሜሪካ መንግሥትና ኤምባሲዋ ላይ የሰነዘሩትን ተቃውሞ በሚመለከት ከአሜሪካ መንግሥትም ሆነ አዲስ አበባ ከሚገኘው ኤምባሲ የተሰጠ ምላሽ የለም። በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫናን እያሳደረ ነው በሚል ወቀሳ የሚሰነዘርበት ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ይህንኑ በመቃወም ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ
ምዕራባውያን አገራት “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይግቡ” የሚሉ ሰልፎች አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙት በአሜሪካና በብሪታኒያ ኤምባሲዎች ፊት ለፊት መካሄዳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ። የተቃውሞ ሰልፉ አገራቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያካሂዱትን ጣልቃ ገብነትና ሐሰተኛ መረጃ ያሰራጫሉ ያሏቸውን መገናኛ ብዙኃንን የሚያወግዝ መሆኑን ፋና ዘግቧል። በሰልፎቹ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት በኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ደብዳቤ ለብታኒያ ኤምባሲ ማስገባታቸው ተነግሯል።