ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጦር ግንባር በመገኘት ዘመቻውን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎ የመንግሥት መደበኛ ሥራዎች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እየተመሩ መሆናቸው ተገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከማክሰኞ ኅዳር 14/2014 ዓ.ም ጀምሮ በጦር ግንባር ተገኝተው አመራር እየሰጡ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኞ ዕለት “ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው” በማለት እራሳቸው የአገሪቱ ሠራዊት በተሰለፈበት ግንባር በመገኘት ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እንደሚዘምቱ ካሳወቁ በኋላ ነው ወደ ጦር ግንባር መሄዳቸው የተገለጸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት መግለጫቸው ላይ በጦር ግንባር በመገኘት ሠራዊቱን በሚመሩበት ጊዜ በመንግሥታቸው ውስጥ የሚፈጠረውን ክፍተት ሌሎቹ የክልልና የፌደራል መንግሥት አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ አቅማቸው እንደሚያከናውኑ ገልጸው ነበር። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት በጦር ግንባር ተገኝተው አመራር እየሰጡ መሆናቸውን እንደተናገሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ጨምረውም የመንግሥት መደበኛ ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ የዕለት ከዕለት ሥራዎች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቶ ደመቀ መኮንን እየተመራ መሆኑንም አመልክተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኞ ምሽት ይፋ ባደረጉት ውሳኔ ላይ “ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” በማለት ሌሎችም እንዲከተሏቸው ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም መሠረት በመንግሥታቸው ውስጥ ያሉ በርካታ ባለሥልጣናት ወደ ጦር ግንባር በመጓዝ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት የገለጹ ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ የአገሪቱ ታዋቂ ሰዎችም ተመሳሳይ ምላሽ እየሰጡ መሆናቸው እየተዘገበ ይገኛል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ ወራት ተቆጥረዋል። በተለይ የህወሓት ኃይሎች በተለይ በአማራ ክልል በኩል የሰሜን ወሎ እና የደቡብ ወሎ ተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ወደ ሰሜን ሸዋ እየተቃረቡ መሆናቸውን ተከትሎ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊቱን እራሳቸው ለመምራት ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት የወሰኑት።
ምንጭ – ቢቢሲ