ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (የቆየ ፎቶ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ የመከላከያ ሠራዊቱ ከአማጺያን ጋር የሚያደርገውን ጦርነት እንደሚመሩ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ምሽት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ኢትዮጵያ የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ ታሪክ አደራ አለብን” በማለት ባሰፈሩት መልዕክት “ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ነው” በማለት እራሳቸው የአገሪቱ ሠራዊት በተሰለፈበት ግንባር በመገኘት ለመምራት “ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለስምንት ወራት ከቆየ በኋላ የአገሪቱ ሠራዊት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ ተዛምቶ ቀጥሏል። ከሰኔ ወር ወዲህ የህወሓት ኃይሎች በተለይ በአማራ ክልል በኩል የሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ተለያዩ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ወደ ሰሜን ሸዋ እየተቃረቡ መሆናቸው በተነገረበት ጊዜ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊቱን ለመምራት ወደጦር ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን ያስታወቁት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም ሌሎችም “ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ” በማለት ሌሎችም የእሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እሳቸው በጦር ግንባር በመገኘት ሠራዊቱን በሚመሩበት ጊዜ በመንግሥታቸው ውስጥ የሚፈጠረውን ክፍተት ሌሎቹ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ አቅማቸው እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

“አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ጠላቶች በውስጥም በውጪም እንደተነሱ ጠቅሰው “ይህ ትግል ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው” ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ “የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጥቃት ለመመከት” ሁሉም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጠይቀዋል።

‘በውጭ ኃይሎች ሴራ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ሕዝቦች ላይ ሁሉ አዲስ የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን ያለመ እንደሆነ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የተሰማው የፓርቲያቸው ብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኞ ዕለት አገሪቱ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ማድረጉ ከተገለጸ በኋላ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ “እያንዳንዱ የብልፅግና አመራር እራሱ ተሰውቶ ኢትዮጵያን ለማዳን ተዘጋጅቷል” በማለት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር አለሙ ስሜ በፓርቲው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከፓርቲው ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጀምሮ ሁሉም የብልጽግና አመራር ወደ ግንባር ተሰማርተው ውጊያዎችን ለመምራት መወሰናቸውን ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ ዶ/ር አለሙ ለሚዲያ በሰጡት ገለጻ መናገራቸውም ሰፍሯል።

“የሚያስፈልገውን ሁሉ መስዕዋትነት ከፍለን ኢትዮጵያን ለማዳን ወስነናል፤ ሁሉም ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይደርገዋል” ብለዋል ዶ/ር አለሙ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለም ወደ ጦር ሜዳ እንደሚዘምቱ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላማዊ መፍትሄ መቋጫ እንዲያገኝ የተለያዩ ወገኖች ግፊት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ ልዩ ተወካይ መድቦ ለማሸማገል ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *