የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ የሚደረግ የትኛውም በረራ ምንም አይነት የደኅንነት ስጋት እንደሌለበት ገለጸ።

ባለሥልጣኑ ይህንን ያለው የአሜሪካ ፌደራል የአየር በረራ አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ረቡዕ ዕለት ባወጣው ማሳሰቢያ ላይ “አውሮፕላኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመሬት ላይ እና/ወይም ከመሬት ወደ አየር ለሚተኮሱ የጦር መሳሪያዎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ” ማለቱን ተከትሎ ነው። ባለሥልጣኑ እንዳለው በአዲስ አበባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ጨምሮ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ የሚያሰጋ ነገር የሌለባቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው ብሏል።

ጨምሮም በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ የሚደረገውን በረራ በተመለከተ የወጣው ማስጠንቀቂያና የተሰራጩት ዘገባዎች “መሠረተ ቢስ እና ከእውነታው ፍጹም የሚቃረኑ ናቸው” ብሏል። ባለሥልጣኑ የአገሪቱን የአየር ክልል እና አየር ማረፊያዎች ደኅንነት የተጠበቀና አስተማማኝነትን የሚያረጋግጥ ሁሉንም አይነት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ለተጠቃሚዎች ማረጋገጥ እንደሚሚወድ ገልጾ ለዚህም አስፈላጊውን ዓለም አቀፍ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሷል።

ከአሜሪካ ፌደራል ኤቪዬሽን ባለሥልጣን በወጣው ማሳሰቢያ ላይ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለአየር በረራ ስጋት እንዳለ በመጥቀስ፤ በተለይ በመሬት ላይ በማረፍና በመነሳት ወቅትን ጨምሮ ዝቅ ባለ ከፍታ የሚጓዙ አውሮፕላኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። አዲስ አበባ በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋነኛ ማዕከል ከመሆኗ በተጨማሪ በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በረራዎችን የሚያካሂዱት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ነው።

የአሜሪካው የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያወጣው ማሳሰቢያ በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ የተከሰተ ነገር ወይም ስጋት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም፣ ነገር ግን ጦርነቱ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክሯል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ግን በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ አካባቢ ለአየር ትራንስፖርት ስጋት የሚሆን ነገር እንደሌለ አመልክቷል።

አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ዜጎቿ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ በተደጋጋሚ ስታሳስብ መቆየቷ ይታወቃል። መንግሥት ግን እንዲህ አይነቱን ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የሚያደርስ የደኅንነት ስጋት በዋና ከተማዋ ውስጥ የለም ሲል ጥሪውን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጎታል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *