የውጭ ዜጎችን በተለየ መልኩ ማዕከል ያደረገ የህግ አፈፃፀም የለም ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡ አምባሳደሩ በሳምንታዊ መግለጫቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እያነሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዋጁ የአገርን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የወጣ ህግ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሩ የውጭ ዜጎችን በተለየ መልኩ ማዕከል ያደረገ የህግ አፈፃፀም አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ እና የጉዞ ሰነድን መጠቀም ይቻላል ብለዋል። ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች የሚያነሷቸው ቅሬታዎች መሰረት ቢስ ናቸው ያሉት አምባሳደር ዲና፥ አሁንም የአገራትን ገፅታ ለማፍረስ የሌለን ነገር ፈጥረው ዜናዎችን እየሰሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የስነ ልቦና ጦርነት እያካሄዱ ነው ሲሉም ነው የገለፁት። አንዳንድ አውሮፓውያን አገራትም በኢትዮጵያ ላይ ግፊት እያደረጉ ሲሆን ከሚዲያዎች ጋር ተጣምረው እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው የኢትዮጵያ መንግስት በዩጋንዳ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት ማውገዙን ጠቅሰዋል። ውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ኢትዮጵያውያኑ በአሜሪካ ከ90 በላይ የሚሆኑ የኮንግረስ አባላትና ባለስልጣናትን ማነጋገራቸውን ለተለየዩ መሪዎች እና ባለስልጣናትም ደብዳቤዎችን በማስገባት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማውገዛቸውን አስረድተዋል።

ስዊዘርላንድ ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ ሉግዘምበርግ፣ ስፔን እና ሌሎች አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዙ ሰልፎችን አካሂዳዋል ብለዋል በመግለጫቸው። በሌላ በኩል ለንደን ያሉ ኢትዮጵያውያን ለሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ 11 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ማሰባሰባቸውን አስታውሰዋል፡፡  በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የኬንያ መንግስት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያንፀባረቀውን አቋም ታደንቃለች ነው ያሉት።

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ጉዳይ አፍሪካዊ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አበረታች ነው ያሉት አምባሳደሩ ሁኔታዎችም ያንን ለማድረግ የሚገፋፋ መሆኑን ነው የተናገሩት። የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የአፍሪካን በጎ ገፅታ ለመገንባት እንደማይሰሩና ይልቁንም የረሃብ እና የጦርነት ጉዳዮችን ብቻ አጀንዳ አድርገው መስራት ላይ እንደሚያተኩሩ ነው የገለፁት፡፡ ስለሆነም የተሳሳተውን ትርክት የሚያቃና የሚዲያ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል በመግለጫቸው።

በሌላ በኩል ሱዳን በአሁኑ ወቅት በራሷ የውስጥ ጉዳይ በመጠመዷ በግድቡም ሆነ በድንበር ጉዳይ ለመወያየት የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለችም ነው ያሉት፡፡ እንዲሁም በጅቡቲ የሚገኘው ወታደራዊ ጄነራል በኢትዮጵያ ዙሪያ ለሚዲያ የሰጡት አስተያየት ፖለቲካዊ ተደርጎ መወሰድ እንደማይችልና የግል አስተሳሰባቸው እንደሆነ ነው ያነሱት።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *