በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ጦርነቱን መግታት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።
እስካሁን ድረስ ስለ ፌልትማን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ውይይት ይዘት ዝርዝር መረጃ ባይወጣም፤ ሮይተርስ የዜና ወኪል የተኩስ አቁም ላይ መድረስን ጨምሮ ሌሎችም ጦርነቱን ማቆም ስለሚቻልባቸው መንገዶች መነጋገራቸውን ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በበኩሉ፤ ፌልትማን ጦርነቱ እንዴት መገታት እንዳለበት የአገራቸውን አቋም ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል ሲል ዘግቧል። አቶ ደመቀ በበኩላቸው የህወሓት ኃይሎች ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲወጣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና መደረግ እንዳለበት በመግለጽ የኢትዮጵያን አቋም ለፌልትማን ማስረዳታቸውን ኢዜአ ጨምሮ ዘግቧል።
ፌልትማን ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይታ የሚያደርጉ ሲሆን ከሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል። ፌልትማን ከኅዳር 9 እስከ ኅዳር 11/2014 ዓ. ም በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት ልዑካንን እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ወኪሎችን እንደሚያነጋግሩ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ፌልትማን ጦርነቱ የሚገታበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል። “ውጊያው ድርድርን ተመርኩዞ ስለሚቆምበት ሁኔታ እንዲሁም ግጭቱ እንዴት ሊቆም እንደሚችል ይወያያሉ” ሲል መግለጫው አትቷል።
“በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እና የሰዎችን ሕይወት የሚያድን ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ማስቻል የአሜሪካ ፍላጎት ነው” ሲልም አክሏል። ትላንት መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ጄፍሪ ፌልትማን “ጦርነቱን አቁሞ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል” ብለዋል።
የኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ መመለስ
የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አድርጎ የሾማቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆም በድጋሚ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር የተገናኙት የአፍሪካ ሕብረት ልዑኩ ኦባሳንጆ፤ ለሰሜኑ ጦርነት መፍትሔ በማበጀት ረገድ የደረሱበትን ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ እየጠበቀች እንደሆነ አምባሳደር ዲና በትላንትናው መግለጫቸው ጠቁመዋል።
ኦባሳንጆ ከሁለት ሳምንታት በፊት የፌደራሉን መንግሥት ባለሥልጣናት እና የህወሓት መሪዎችን ካነጋገሩ በኋላ በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለውን ፍላጎት ለመረዳት የሚያስችል መረጃ እንዳገኙ መግለጻቸው ይታወሳል። ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ መሰጠት እንዳለበትም ኦባሳንጆ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ትናንት በማኅበራዊ ድረ ገጹ ኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ጠቅሶ፤ ልዑኩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተገናኝተው መፍትሔ በማፈላለግ ሂደታቸው የደረሱበትን ሐሳብ ይገልጻሉ ብሏል። መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሕብረት አምባሳደሮች ማብራሪያ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።
ምንጭ – ቢቢሲ