የ72 ዓመቱ አዛውንት አቦይ ተክለ ኪዳን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከ40 ዓመታት በላይ ኖረዋል። ከበኩር ልጃቸው ውጪ ያሉት ስድስት ልጆቻቸው ተወልደው ያደጉትም አዲስ አበባ ነው።
ከአስር ዓመት በፊት ጡረታ ወጥተው በግል የትራንስፖርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር። እድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ደግሞ ከትዳር አጋራቸው ጋር ቆርበው ብዙ ጊዜያቸውንም ቤታቸው እና ቤተ ክርስቲያን እንደሚያሳልፉ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ። ከሳምንት በፊት ግን ከአስር በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት ቤታቸው ድረስ በመምጣት እንደሚፈለጉ ገልጸው “ቤቱን ፈትሸው ምንም ነገር ሳያገኙ፣ እያንገላቱ ወሰዷቸው” ሲል ልጃቸው ገልጿል። “በተወለድኩባት እና አገሬ በምላት ከተማ እንደዚህ አይነት ነገር አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም” ይላል ልጃቸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና እስር
ከተጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይ አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎች መታወቂያ ይዘው እንዲንቀሳቀሱና በፀጥታ ኃይሎች ሲጠየቁ እንዲያቀርቡ የሚስገድድ ሲሆን፣ በተለይ ከአዋጁ ተግባራዊ መሆን በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ለእስር መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመብት ተቆርቋሪዎች አስሩ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው ቢሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ”እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከሽብር ቡድን ግንኙነት ባላቸው ላይ ሲሆን፣ በዚህም እየተያዙ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደሉ” በማለት ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በዚህ የእስር ሂደት ውስጥ ታዋቂ ሰዎችና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት አመልክቶ፤ ከእነዚህም መካከል ዳንኤል ተክሌ የተባሉ የአንበሳ ባንክ ፕሬዝዳንትና አምስት ሠራተኞች ታሰረው መለቀቃቸውን ዘግቧል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እንዳሉት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ “ለአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ድጋፍ በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንጂ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስራት አልተፈጸመም” ማለታቸው ተዘግቧል። ሚኒስትሩ ጨምረውም በአዲስ አበባ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጆ እንደሚኖሩ እንደሚገመት አመለክተው “የታሰሩት ከአንድ ሺህ የማይበልጡ ናቸው” ብለዋል።
“እናታችን እያሉ እያለቀሱ ነው“
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገረው አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ወጣት ከ10 ዓመት በላይ በፌደራል ፖሊስ ያገለገለች እና በሰንዳፋ የፌደራል ፖሊስ ኮሌጅ መምህር የነበረች አክስቱ እንደተያዘች ይገልጻል። “ከሁለት ወር በፊት እሷ እና ሌሎች የትግራይ ተወላጆች ‘ለስልጠና እንፈልጋችኋለን’ ብለው ወስደው ለ20 ቀናት ሰንዳፋ በሚገኝ የስልጠና ማዕከል ካቆይዋቸው በኋላ ወደ ጦላይ ወሰዷቸው” ይላል።
ትዕግስቲ [ስሟ ተቀይሯል] ስትሆን ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ናት። የሰባት እና የአራት ዓመት ልጆቿ’ ‘እናታችን’ እያሉ እያለቀሱ ነው” በማለት ህጻናት ልጆቿ እያስቸገሩ መሆናቸውን ይናገራል። የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በመከላከያ፣በ ፌደራል ፖሊስና በደኅንነት ተቋም ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሥራ እንዲያቆሙ እንደተደረጉና አብዛኞቹ በተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ “ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው” የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበውም በተወሰኑት ላይ እስር ተፈርዶባቸዋል።

‘ገንዘብ የሚጠይቁ አሉ‘
በመንግሥት ሆስፒታል የልብ ህክምና ዶክተር ሁኖ የሚሰራው ወንድሙ የታጠቁ ፖሊሶች እና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎች ሥራ ቦታው መጥተው እንደወሰዱት የሚናገረው ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ግለሰብ ወንድሙ “ከማንነቱ በስተቀር ምንም አይነት ጥፋት የለበትም” ብሎ ያምናል።
”ከጁንታ ጋር ግንኙነት እንዳለህ ጠርጥረናል” ብለው እያንገላቱ መጀመሪያ ወደ ገርጂ ቆይተው ወደ ለገሀር ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱት ይናገራል። “አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያናገርነው” የሚለው የታሳሪው ወንድም፣ ፖሊስ በቅርብ ሆኖ ስለሚያዳምጥ ”ደህና ነኝ” ከማለት ውጪ ስለተፈጠረው ነገር መናገር እንዳልቻለ ገልጿል። የሐኪሙ ወንድም የተያዘበት እና አዛውንት አባቱ የታሰሩበት አርቲስት ለማስፈታት ገንዘብ የሚፈልጉ እንዳሉ፣ ከፍለው የተፈቱ እንዲሁም ከፍተኛ ከንዘብ የተጠየቁ ሰዎች እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በማስፈራራት እንዲሁም የታሰሩ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ ለመቀበል የሞከሩ አምስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ክስተት በጥቂት ግለሰቦች የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊት በመሆኑ የአጠቃላዩን የፖሊስ አባል የሚወክል አለመሆኑንና እንዲህ አይነቱን ተግባር “እንደ ተራ ወንጀል አናየውም። አገር እንደመክዳት ነው የምንቆጥረው” ብለዋል።
‘እስር ቤቶች ሞልተዋል’
የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አንዳንዶቹም የብሔሩ ተወላጅ መሆናቸው እንኳን የማያውቁ ቤተሰቦች ከነልጆቻቸው በጅምላ መታሰራቸው እና መጉላላታቸውን ጎረቤቶቻቸው ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጠው መግለጫ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው እስራት እናቶች እና ህጻናት እንደሚጨምር እና ማንነት መሰረት ያደረገ እንድሚመስል ጠቅሷል። ቢቢሲ ያነጋራቸው ሰዎች ከታሰሩ ቤተሰቦቻቸው እስካሁን ፍርድ ቤት የቀረበ እንደሌለ ይናገራሉ።
እስር ቤቶች በመሙላታቸው ብዙ ሰዎች በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ እና መጋዝኖች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚገኙ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። ብዙ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው የት እንደታሰሩ የማያውቁ ሲሆን አንዳንዶቹ አፋር ክልል ወደ ሚገኘው አዋሽ አርባና ወደ ሰንዳፋ መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ኮማንደር ፋሲካው እስካሁን አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ሰው አንደታሰረ መረጃ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ መለቀቃቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የገለጸ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ የታሳሪዎቹ ቁጥር ቢያንስ አንድ ሺህ እንደሚሆን አመልክቷል። እስሩ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ የሚፈጸም አለመሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እስሩ እንዳሳሰበው በሰጠው መግለጫ ላይ በተለያዩ ስፍራዎች እየተፈጸመ መሆኑን አመክልቷል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ እስሮች መበራከታቸው ተቋሙን እንዳሳሰበውና አስሩ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር እና በሌሎች ስፍራዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ እና በርካታ ሰዎችን እያሰረ ነው ብለዋል።
‘ያልፋል’
የፌደራል ፖሊስ አባል የነበረችው ታሳሪ አድዋ ከተማ የተወለደች ሲሆን፣ የአንድ ልጅ አባት የሆነው ዶክተር ግን አዲስ አበባ ተወልዶ ማደጉን ዘመዱ ይናገራል። “ለረጅም ጊዜ እዚህ ከተማ ውስጥ ነው የኖርነው፤ እርግጥ ትግራይ ውስጥም ቤተሰቦች አሉን። ተጋሩ መሆናችንም እናውቃለን፤ ጎረቤቶቻችንም ያውቃሉ። ማንነታችን ደብቀን አልኖርንም። እንዲህ አይነት ነገር ይመጣል ብለንም አስበን አናውቅም” ይላል።
በተጨማሪ “ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ባለው አንድ ዓመት ትግራይና ተጋሩን በተመለከተ የሚነገሩ ነገሮች ደስ አይሉም። ከቅርብ ጓደኞቼ የደረሰብኝ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ብዙ የተንገላቱ ቤተሰቦች አሉኝ” በማለት የተፈጠረበትን መጥፎ ስሜት ይገልጻል። አብዛኞቹ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታሳሪዎች ቤተሰቦች ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ “እንደምንም ያልፋል” የሚል በሚል ተስፋ አላቸው።
ምንጭ – ቢቢሲ