የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ሰዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉበት ሁኔታ እና የእስረኞች አያያዝ አፋጣኝ ትኩረት ያስፈልገዋል አለ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ከአዋጁ በኋላ ሰዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉበት ሁኔታን፣ አያያዛቸውን እና መስተካከል አለባቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሐሳቦቹን አስቀምጧል።

‘መረጃ ማሰባሰብ አልተቻለም’

ኮሚሽኑ በፖሊስ ጣቢያዎችንና ማቆያዎችን በመጎብኘት፣ ታሳሪዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በማነጋገር፣ በተለያዩ ደረጃ ካሉ የፖሊስ አባላት እና አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ መረጃ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጿል። ይሁን እንጂ ኢሰመኮ የሰዎችን አያያዝ እና የእስር ሁኔታ በሚመለከት መረጃ ለማሰባሰብ በሚያደርገው ጥረት እክሎች እንደገጠሙት አመልክቷል።

በአዲስ አበባ በአምስት ክፍለ ከተሞች ባለሥልጣናት ‘ከላይ ትዕዛዝ ካልመጣልን መረጃ አንሰጥም’ በማለታቸው ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ እክል ሆነዋል ብሏል።

የታሳሪዎች ብዛት

ኮሚሽኑ ከአዋጁ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ አልተቻለኝም ብሏል። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ 714 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል። በሌሎችም ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ እስሮች ሲከናወኑ ስለነበርና እና ሰዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ተግባር በመቀጠሉ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይታሰሩ አይቀርም ብሏል። እንደ ኮሚሽኑ ከሆነ በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል።

የትግራይ ተወላጆች እስር

ኢሰመኮ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ከሚውሉባቸው ምክንያቶች አንዱ በሰዎች ጥቆማ መሆኑን ገልጿል። “አብዛኞቹ ግን ከኅብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉና ከመካከላቸው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።”

ኮሚሽኑ ብሔር ተኮር እስር ስለመከናወኑ ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥያቄ አቅርቦ ያገኘው ምላሽ፤ “ሰዎች የሚያዙት በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ተጠርጥረው እንደሆነና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁለቱም ድርጅቶች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመሆናቸው አኳያ የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር ሊመስሉ እንደሚችሉ” የሚል መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

የእስረኞች አያያዝ

ኮሚሸኑ እድሜያቸው 80 የሚደርስ አረጋውያንን ጨምሮ፣ የሚያጠቡ ሴቶች፣ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው፣ ተከታታይ ሕክምና ያሚያስፈልጋቸው ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ሰዎች ጭምር በቁጥጥር ስለመዋላቸውን የክትትል ቡድኑ አመልክቷል ይላል።

“አንዳንዶቹ ጣቢያዎች እና የማቆያ ስፍራዎች በጣም የተጣበቡ፣ በቂ መፀዳጃ የሌላቸው እና በቂ አየር እና ብርሃን የማያገኙ ናቸው። ለምሳሌ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አረጋውያንንና የአእምሮ ህመምተኛ እንደሆኑ የሚነገር ሰዎችን ጨምሮ 241 ሰዎች ስፋቱ 20 ሜትር በ10 ሜትር ብቻ በሚገመት አንድ የወጣቶች ሁለገብ አዳራሽ ተይዘው አንድ መፀዳጃ ቤት ለመጋራት ተገደዋል” ይላል የኢሰመኮ መግለጫ።

‘ሰዎች የተያዙበትን ምክንያት አያውቁም’

ኮሚሽኑ ያነጋገርኳቸው አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ተጠርጥረው የተያዙበትን ምክንያት እንደማያውቁ እና ፖሊስ ለምን እንዳስራቸው እንዳልነገራቸው ገልጸውልኛል ብሏል። የአብኞቹ ታሳሪዎችም ቅሬታም የተያዙት “በብሔራቸው ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ” ይላል ኮሚሽኑ።

ምክረ ሳቦች

ኮሚሽኑ ሕግ አስከባሪ አካላት በአፋጣኝ መተግበር አለባቸው ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች ለግሷል። “ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖሩን የሚያረጋገጥ መረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች ፣ . . . አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች እና የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር ይለቀቁ” ብሏል።

ማንኛውም እስር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መንፈስ በመረዳት በተመጣጣኝነት፣ በጥብቅ አስፈላጊነታቸው እና ከመድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ መከናወን አለባቸው ሲል ኮሚሽኑ ጨምሯል። ከዚህ በተጨማሪም የታሳሪዎች አያያዘ እንዲሻሻል ጠይቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

በሰሜን ኢትዮጵያ እተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ “በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ፣ ይህንን አደጋ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ” ከሁለት ሳምንታት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ መደንገጉ ይታወሳል።

ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ በመላዋ አገሪቱ ተፈፃሚ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታወጀ ሲሆን ከቀናት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ተደርጓል። ከዚህ በኋላም ከተከሰቱ አስሮች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *