በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት አገሪቷን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት ነው ሲሉ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።

ረቡዕ እለት ከኬንያ በጀመሩት ጉብኝትም በቅርቡ ኢትዮጵያ መጥተው ከነበሩት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስባቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው ብለዋል። ኬንያ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባላት ቦታም ሆነ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ በአካል ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘት እያደረጉት ላለው የሰላም ጥረት አንቶኒ ብሊንከን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭም አገራቸው ከኬንያ፣ ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ከሌሎች አጋሮች በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን በዛሬው ዕለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስረድተዋል።

በተለይም ይህንን በተመለከተ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከከፍተኛው ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በመሆን ተፋላሚ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በረሃብ ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖችን ህይወት የማዳን እርዳታ እንዲመቻችና ሰብዓዊ አገልግሎቶች እንዲደርሱ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጦርነቱ እየሰፋ በሄደ ቁጥርም አደጋ ላይ የሚወድቀው የዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በትግራይ እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልል ያለው ሕዝብ ለስቃይ መዳረጉን ጠቅሰዋል። የሕዝብ ስቃይን ለማቆምና የሚፈልጉትን እርዳታ እንዲያገኙም ውይይቶች መጀመራቸውን ማረጋጋጥ የአገራቸው አቋም መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ መሆኑን በማስረዳት ይህም ለአሜሪካ፣ ለጎረቤት አገር ኬንያም ሆነ አጋሮች ላሏቸው ትልቅ ስጋት ነው ብለዋል። ሁሉም ወገኖች ከጦርነት እንዲታቀቡ በዚሁ ወቅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ህወሓትና የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ መግታት አለባቸውም ብለዋል። አሜሪካ ጦርነቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መዛመቱን ቀጥሎ ዜጎቿም እንዲወጡ በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥታለች።

ይህንንም አስመልክቶ የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞችን ለመቀነስ ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ አገራቸው ብትወስድም ኤምባሲያቸው አሁንም ጥረቶችን እንደሚደግፍና በአገሪቱ ላሉ ለአሜሪካ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ መሉ በሙሉ አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ሆኖም አንቶኒ ብሊንከን በዚህ አጋጣሚም ለሳምንታት ያህል አገራቸው አጽንኦት ሰጥታ እንደጠየቀችው በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም የአሜሪካ ዜጎች ያሉትን አማራጮች በመጠቀም ከአገር እንዲወጡ አሳስበዋል።

ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

የአሜሪካ ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚያስጠነቅቅ የጉዞ ማሳሰቢያው ጋር ተያይዞም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ጥያቄ አሜሪካ ይህንን ማስጠንቀቂያ ማውጣቷ ሁኔታው ምን ያህል አደገኛ እንደሆነና ግጭቶችን ለማስቆም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ያመለክት ይሆን? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

አንቶኒ ብሊንከንም ለዚህም የሰጡት ምላሽ በአገሪቱ እየተስፋፋ የሄደው ጦርነት በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና ይህም በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ መደቀኑን አስረድተዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በዋነኝነት የአገራቸው ኃላፊነት ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ዜጎች፣ የኤምባሲ ሠራተኞች ደኅንነት እና ጥንቃቄ መሆኑን ገልጸው ያንንም እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አሜሪካውያን ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ለቀው እንዲወጡ በማሳሰብ ለአሁኑ ደኅንነታቸው ላይ ቅድሚያ በመስጠት ነገሮች ሲስተካከሉ እንደሚመለሱ “ጠንካራ ተስፋ እና ፅኑ እምነት አለኝ፤ ኢትዮጵያ ወደፊት እንድትራመድ ወደሚቻልበት ቦታ እናግዛቸዋለን” ብለዋል።

“ነገር ግን በዋነኝነት ጥንቃቄና ደኅንነት ለዜጎቻችን ኃላፊነት አለብን። ኤምባሲው ከቀናት በፊት የሰው ኃይል እንዲቀንስ መመሪያ ሰጥተናል” በማለት አስረድተዋል።

ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ተፋላሚ ኃይሎች ላይ ልትጥለው የነበረውን ማዕቀብ ወደ ተኩስ አቁም እና ውይይት እንዲገቡ ዕድል ለመስጠትም በሚል ገታ ተደርጓል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች በሰብአዊ መብት ጥሰቶች መከሰሳቸውን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ የትግራይ ተወላጆች በጸጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን በመጥቀስ፤ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ለማድረግ ከዲፕሎማሲያዊ ንግግር በላይ ምን መደረግ አለበት? የሚል ጥያቄም ተጠይቀው ነበር።

ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ቆም ብለው እንዲያስቡ፣ እንዲነጋገሩና ሰብዓዊ እርዳታ ለሕዝባቸው እንዲደርስ እና በመጨረሻም በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተገኝተው እንዲደራደሩ የሚያስችል ዕድል አለ፤ ከዕድልም በላይ ልዩነታቸውን መፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከቀናትም በፊት ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ለሰላም ምን አይነት ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውንም አውስተዋል።

ጦርነቱ እየፈጠረ ያሉትን ጥልቅ ስጋት እንደተጋሩም ገልጸው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱ እንዲቆም፣ ሁሉም አካላት በአስቸኳይ እንዲደራደሩ እንዲሁም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አፋጣኝና ያለምንም እንቅፋት ሰብአዊ እርዳታ መድረስ አስፈላጊነቱንም በማስመር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

“የሰብዓዊ ዕርዳታ በነፃነት ሲደርስ ማየት፣ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዲመጡ፣ የታሰሩ ሰዎች ሲፈቱ ማየት እንፈልጋለን፣ እና የተፈጠረው ልዩነት በሰላማዊና በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉም ሲረባረብ ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።

አክለውም “ዋናው ነገር ለዚህ ግጭት ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሄ የለም። እያንዳንዱ አካል ያንን ተገንዝቦ እርምጃ መውሰድ አለበት” በማለት ብሊንከን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ከሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ጋር ተያይዞ ላለፉት ወራት አገራቸው ስታሳስብ እንደነበረችና ከፍተኛ ስጋት እንዳጫረባቸው ጠቅሰው በቅርበት እየተመለከቱት መሆኑንና በጥንቃቄም እያዩት መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚሀም ጋር ተያይዞ በትግራይ የተፈጸመው ጥሰት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ብላ አገራቸው ታስብ እንደሆነና ከሆነም ለምን ዝምታ ተመረጠ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ ምን ተብሎ መጠራት እንዳለባቸው ለመወሰን ሕግና ያሉትን ሀቆች በመመርመር የሚወሰን ይሆናል ብለዋል።

“ጥሰቶቹ ምንም ተብለው ቢጠሩ ግፎች መፈጸማቸውን ቀጥለዋል። የሰዎች ስቃይ መቆም አለበት። ለተፈጸሙ ጥሰቶችም ተጠያቂነት መስፈን ያስፈልገዋል። ይህ ተጠያቂነት እንዲኖርም ቁርጠኞች ነን” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ሕጋዊ መሪ ናቸው፤ ከዚህ አንጻር የዐቢይን ከሥልጣን በኃይል ለማውረድ የሚፈልገውን ህወሓትን እንዴት ያዩታል? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥያቄ በቀጥታ ባይመልሱም ያሉት ግጭቱ መፈታት ያለበት በመነጋገርና በመደራደር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም በሕገ መንግሥታዊ ሥስርዓቱ መሰረት መደረግ አለበት ብለዋል።

በአገሪቱ የተመረጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ቅሬታ ያለባቸው አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነቶቻቸውን ሊፈቱ እንደሚገባም አስምረዋል።

“እንደ አለመታደል ሆኖ ሁሉም አካላት ያለውን የፖለቲካ ሂደት ከመጠቀም በተቃራኒ በወታደራዊ መንገድ መጠቀምን መርጠዋል። ልዩነቶችን ለመፍታት እና ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ ሁሉም አካላት ወደ ፖለቲካው ሂደት መመለስ አስፈላጊ ነው” በማለትም አስረድተዋል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ደርሰው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝተው የነበሩት የፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጉብኝት አስመልክቶ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ደርሰው ከተመለሱ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስፋ አለው ብለው ያምናሉ ወይ የሚል ነበር።

በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው የነበሩት የኬንያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬቸል ኦማሞ በበኩላቸው አገራቸው ኬንያ ይህንን ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ወዳጅና ጎረቤትነቷ ነው የምትመለከተው ብለዋል።

“ወዳጆች እና ጎረቤቶች ለዚህ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ያምናሉ። የተኩስ ማቆም ይቻላል ብለን እናምናለን። ሌሎች የሰብአዊ እርዳታን በተመለከተ መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እናምናለን። የኢትዮጵያን ሕዝብ ፅናት እና ጥበብ ማመን አለብን ምክንያቱም በመጨረሻ መፍትሄው የሚመጣው ከእነሱ ነው” ብለዋል።

አክለውም “እንደ ጎረቤት ማድረግ ያለብን መደገፍ፣ መመካከር፣ እጅ ለእጅ መያያዝ፣ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መጠቆም ነው። ይህ ቀውስ ሲቋጭ፣ እንደሚያከትም እናምናለን፣ ኢትዮጵያን የበለጠ ጠንካራ አገር፣ ጠንካራ አጋር እንድትሆን ያደርጋታል። ኢትዮጵያ ተመልሳ ለቀጠናችን ሰላም ዋስትና የምትቆም ትሆናለች። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተስፋ አንቆርጥም። እናም አዎንታዊ በሆነ መልኩ መቀጠል አለብን ይህንንም ቀውስ ለመፍታት ጸንተን መቆየት አለብን” ብለዋል።