የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው አገሪቱ ከታወጀ በኋላ በአዲስ አበባ ውስጥ ለሕገወጥ ድርጊት ሊውሉ ነበር ያላቸውን የተለያዩ ጦር መሳሪያዎችና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መያዙን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ በተደረገው ክትትልና ፍተሻ ነው” በከተማዋ ውስጥ የጦር መሳሪያዎች፣ ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶች መያዙን የገለጹት።

በዚህም መሠረት ከጥቅምት 23 አስከ 30 በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ በፖሊስ በተደረጉ ክትትልና ፍተሻዎች ከ580 በላይ ሕገወጥ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችን፣ ከ600 በላይ ሽጉጦች እንዲሁም በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር መዋላቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከአራት ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ ወደ 40 ሺህ የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር፣ የመገናኛ ሬዲዮና የሳተላይት ስልክ፣ የተለያዩ ወታደራዊና የፖሊስ አልባሳትና ቁሳቁሶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎችና ፓስፖርቶች እንዲሁም “ሌሎች ለሽብር ድርጊት ሊውሉ ነበር የተባሉ ነገሮችም” መያዛቸውን ኮማንደር ፋሲካው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፖሊስ እያደረገ ባለው ክትትልና በሚወስደው እርምጃ “አዲስ አበባ ውስጥ ሊፈጸሙ የነበሩ የተለያዩ ከባድ ድርጊቶችን መቆጣጠሩንና እንዳይፈጸሙ ለማድረግ ተችሏል” ብለዋል። ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም በመላው አገሪቱ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ እየተደረገ ባለው ክትትልና ፍተሻ ነው የተለያዩ ቁሳቁሶችና ተጠርጣሪ ግለሰቦች እየተያዙ ያሉት።

በቁጥጥር ስር እዋሉ ስላሉ ሰዎች

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ረቡዕ እለት ባወጣው ሪፖርት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ከመካከላቸውም የትግራይ ተወላጆች የሆኑት ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል።

ይህንን በተመለከተ የከተማዋ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “እስሩ የትግራይ ተወላጅ ብቻ በመሆን የተፈጸመ እንዳልሆነና በሚደረግ ክትትልና ጥቆማ መሰረት በሚገኝ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ነው” ብለዋል። “የሌላም ብሔር ተወላጆች ቢሆኑ የሽብር ቡድኑ ተልዕኮ ወስደው፣ ገንዘብ ተከፍሏቸው ሥልጠና ተሰጥቷቸው፣ አንዳንዶቹም መሳሪያ ጭምር ታጥቀው በከተማዋ ውስጥ ሽብር ለመፍጠር የተዘጋጁትን ነው እየያዝን ያለነው።”

በዚህ መካከል ግን ንጹሐን በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደሚችሉ የጠቀሱት ኃላፊው እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሲከሰትም፣ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ከፌደራል መንግሥቱ ተቋማት የተወጣጣው ኮማንድ ፖስት አስፈላጊውን ማጣራት እያደረገ ንጹህ የሆኑ ሰዎች እየተለቀቁ መሆኑን አስረድተዋል።

“ስለዚህም እርምጃው የሚወሰደው የትግራይ ብሔር አባላት ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሽብር ቡድኑ ተልዕኮ ፈጻሚ ሆነው የተገኙ ሌሎችም ሰዎች በፖሊስ ተይዘዋል። እርምጃው በማንነት ላይ ያነጣጠረ አይደለም” በማለት በሁሉም መስክ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ በፖሊስ ትኩረት ውስጥ መግባታቸውን አመልክተዋል።

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መሆኗን በመጥቀስም በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ላይ መደበኛው የሕግ አካሄድ ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታ እንደሌለ ያመለከቱት ኮማንደር ፋሲካው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

“በዚህም ንጹሐኑን ከሕገወጦች በመለየት የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ዕኩይ አላማ ተቀብለው ለመፈጸምና ለማስፈጸም በተሰማሩት ላይ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እርምጃ እየተወሰደ ነው” ብለዋል ኮማንደር ፋሲካው። ከጥቆማና ክትትል እንዲሁም በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰዎች ጋር በተያያዘ በማስፈራራት እንዲሁም የታሰሩ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ ለመቀበል የሞከሩ አምስት የፖሊስ አባላት፣ በሂደቱ የተሳተፉ ደላሎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታም በስፋት የሚፈጸም ድርጊት አለመሆኑን የጠቀሱት ኮማንደር ፋሲካው፤ በጥቂት ግለሰቦች ሕገወጥ ድርጊት የአጠቃላዩ የፖሊስ አባል ስም መነሳት የለበትም በማለት ከዚህም በኋላ በመከታተል እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ተይዘው ያሉበት ሁኔታ የተጨናነቀና አመቺ አለመሆኑን በመግለጽ በቶሎ የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲፈለግ ጠይቋል።

ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት ኮማንደር ፋሲካው በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የማረፊያ ቤቶች የሚታወቁ መሆናቸውንና በዚህም የቦታ ጥበት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸው “ለዚህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ሰዎች በጠባብ ክፍል እንዳይታሰሩና አስፈላጊው አገልግሎቶች እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ “ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ማዋልና አዋጁ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ውስጥ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ” ማድረግ እንደሚቻል ይደነግጋል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን በሚመለከት ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ላይ “በጥቆማ ብቻ የተያዙ ሰዎች አዋጁ በሚጠይቀው መሰረት ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖሩን የሚያረጋገጥ መረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች፣ በተለይም አረጋውያን፣ የሚያጠቡ እናቶች እና የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ” ጠይቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *