ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የማጭበርበር ጦርነት መሆኑን፣ በዚህ ጦርት መሠረታዊ ፈተና ጥይቱ ሳይሆን ወሬው ነው አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ያሉት ኅዳር ሐሙስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ ‹‹የህልውና ጥሪና አገርን የማዳን ርብርብ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ውይይት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው ጦርነት ባህርይ በ1983 ተካሂዷል ብለው፣ ከአዲስ አበባ በ100 እና በ200 ኪሎ ሜትር ክበብ ውስጥ ውጊያ ሳይሆን ፕሮፓጋንዳ ነው የነበረው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ጥናት ቢደረግ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከአገር እንዲወጡ የተደረገው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል በማለት፣ ተመሳሳይ ድርጊት አሁንም እንዲደገም እየተሞከረ እንዳለ ጠቁማዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን አዲስ ታሪክ ባይሠራ፣ ከ1983 ዓ.ም. እንማራለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ ሌላ አገር የለንም፣ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ያለብን ፈተና የወገንን መረጃ የማቀበል ነው፡፡ ባልተገባ መንገድ የወገንን መረጃ ለጠላት መስጠት አይገባም፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ‹‹የጠላትን ፕሮፓጋንዳ›› ባለማወቅ ከማስተጋባት መቆጠብ ያሻልም ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹የእኛ ግብ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ ለቅርብም ለሩቅም ጠላቶች ማሳየት፣ ኢትዮጵያ እንደማትሸነፍና ሽንፈት ታሪካችን እንዳልሆነ ማሳየት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ሰላምና ዕፎይታ እንዲመጣ መሥራት ነው፤›› በማለት፣ ‹‹አሁን ያለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያን በዓለት ላይ ለማቆም የሚደረግ የአገር ግንባታ ሒደት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ አንዱ ተናጋሪ የነበሩት ቢቂላ ሁሪሶ (ዶ/ር)፣ ጦርነቱ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በጋራ ጥምረት የተፈጠረ እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ደካማና ልፍስፍስ አገር እንድትሆነ የሚፈልጉ አገሮች በጋራ የቀረፁት ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕወሓት ከሥልጣን ከተገፋ በኋላ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማፈራረስ ሥራ ላይ ተጠምዶ ነው የቆየው ብለዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን የዛሬ 127 ዓመት በዓድዋ ድል የታየውን መሰል አርበኝነት አሳይተው፣ ኢትዮጵያ የማትፈርስ አገር መሆኗን አስመስክረዋል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው፣ የተሳሳተ የጦርነት መረጃ ማሠራጨት የሕወሓት አንዱ ስትራቴጂ ነው ብለው፣ ለሚጻፉና ለሚነገሩ ጉዳዮች ምላሽ መስጠትና ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማስረዳት ያስፈልጋል ሲሉም አውስተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሕዝቡ በየአካባቢው በመደራጀት አካባቢውን መጠበቅና ፀጉረ ልውጦችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ያሳሰቡ ሲሆን፣ የተበተነ ኃይል ብዙም ቢሆን ትንሽ ኃይል ሊያሸንፈው ይችላል ብለዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር