በአማራ ክልል በህወሃት አማጺያን ለወራት ተይዘው በሚገኙ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ አለማድረጋቸውን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገለጸ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን የሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ እና ሌሎች አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ ባለመድረሱ በመድኃኒትና በምግብ እጥረት የሰዎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። “በገቡት ቃል መሠረት የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት በህወሓት በተያዙ ቦታዎች ላሉ ዜጎቻችን እርዳታ እንዲደረግ ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ቢነጋገሩም ጠብ ያለ ነገር የለም” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ እያሱ በሰብዓዊ እርዳታ እጥረት ንጹሃን እየተጎዱ መሆኑን እና በዋግ ኽምራ ውስጥ 11 ሰዎች በምግብ እና በመድኃኒት እጦት ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ ባሕር ዳር ከተማ የገቡና የአካባቢው ኃላፊዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በርካታ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ መሆኑንና ላለፉት አራት ወራት ምንም ዓይነት እርዳታ ወደ አካባቢው እንዳልደረሰ ገልጸዋል።

“ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገቡት ስምምነት ከአድሏዊ አሰራር ወጥተው ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትን ምክንያት ባደረገ አግባብ ለእነዚህ ዜጎች ምግብ እና መድኃኒት እንዲያደርሱ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። እንደ አቶ እያሱ የዓለም ምግብ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርባላሁ ባለባቸው ቦታዎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርበው የተለየ ድርጅት፣ ትራንስፖርት የሚሰራው እና ደኅንነት ላይ የሚሰራ የተለያዩ ድርጅቶች በመሆናቸው “አንዱ በአንዱ ላይ ምክንያት እየፈጠረ እስካሁን እርዳታ ተደራሽ አልተደረገም” በማለት ያስረዳሉ።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ እያሱ፤ እስካሁን 2.1 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙም አስረድተዋል። እንደ አቶ እያሱ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀል የጀመሩት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን በትግራይ ጦርነት ምክንያት ብቻ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 1.1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ መሆኑን ይናገራሉ። አቶ እያሱ የተፈናቀሉ ሰዎችም በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በ32 መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸው፤ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረስ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

አቶ እያሱ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በ32 ጊዜያዊ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተናግረው፤ ከፍተኛው ቁጥር ያለው ተፈናቃይ የሚገኘው ግን በማኅብረሰቡ ውስጥ መሆኑን ያብራራሉ። “በርካታ ቦታዎች ተፈናቃዮች አሉ። 98 በመቶ የሚሆኑት በማኅብረሰቡ ውስጥ ከዘመድ ተጠግተው የሚገኙ ሲሆን 2 በመቶው ተፈናቃዮች በጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።” በፌደራሉ መንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ቦታዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች መንግሥት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የተለያዩ ድጋፎች እያደረጉ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በህወሓት ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች 5 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የሚናገሩት አቶ እያሱ፤ በአማራ ክልል ‘የደሃ ደሃ’ ተብለው ዕለታዊ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 1.89 ሚሊዮን ተረጂዎች እንደሚገኙም አስታውሰዋል። በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ ክልል በተስፋፋው ጦርነት ሳቢያ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እርዳታን የሚጠብቁ ሲሆን በህወሓት ኃይሎች በተያዙ ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎች ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑን ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰኞ እንዳስታወቀው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ መመደቡን አስታውቋል።