ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ኬንያን ጨምሮ በሦስት አገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት የኬንያው ፕሬዝዳንት ትናንት እሁድ አዲስ አበባ መግባታቸው ተነግሯል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አዲስ አበባ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ጉብኝቱን በማስመልከት ኡሁሩ ኬንያታ ፕሬዝዳንቷንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመጥቀስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አመልክቷል።
ኬንያታ እሁድ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ለሰዓታት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ማምሻውን ወደ ናይሮቢ መመለሳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። እስካሁን ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከኬንያ በኩል መሪዎቹ ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች የተባለ ነገር የለም። ቢሆንም ግን ዋነኛ ጉዳይ ሊሆን የሚችለው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ቀውስ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በተለይ ደግሞ የፕሬዝዳንት ኬንያታ ጉብኝት ዛሬ ወደ አፍሪካ ከሚመጡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጉብኝት ቀደም ብሎ መደረጉ ከብሊንከን ጉብኝት ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ዛሬ በሚጀምሩት የሦስት የአፍሪካ አገራት ጉብኝታቸው ወደ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ሴኔጋል እንደሚጓዙ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ የስድስት ቀናት ጉብኝት ከናይሮቢ እንደሚጀምር የሚጠበቅ ሲሆን ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በሱዳን ያሉ ጉዳዮችን ጨምሮ በሌሎችም ርዕሶች ላይ ይወያያሉ ተብሏል። ኬንያ በአፍሪካ ቀንድና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ካሉ አገራት መካከል የተረጋጋችና በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ ስትሆን፤ በአካባቢው አገራት መካከል በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላት አገር ናት።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአካባቢው ስላለው ቀውስ ከኬንያ ፕሬዝዳንት ጋር ሲመክሩ የነበረ ሲሆን፤ በቅርቡም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ዋሽንግተንን ጎብኝተው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ከዚህ በሻገርም የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን ለቀናት በአዲስ አበባ ቆይተው በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ በማስመልከት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ለሁለት ቀናት ወደ ናይሮቢ ተጉዘው ነበር።
የኦባሳንጆ ጥረት
በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችና በህወሓት አማጺያን መካከል እየተካሄደ ላለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችል አስማሚ ሐሳብ ሊገኝ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ገልጸዋል። አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ችግሩ በንግግር መፍትሄ እንዲገኝለት በአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የተሰየሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የህወሓት መሪዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስቀማጣቸውን አመልክተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካዩ አስካሁን ስላከናወኗቸው ተግባራትና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች በሕብረቱ በኩል በወጣው መግለጫ፤ ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናትና ከትግራይ አመራሮች ጋር ካደረጉት ንግግር በተጨማሪ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል መሪዎች ጋር አበረታች ውይይት እንዳደረጉ ጠቅሰው በቀጣይም ከአፋር ክልል መሪዎች ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል። ከዚህ በሻገርም የአካባቢው አገራት ከሆኑት ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከጂቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሱዳን መሪዎች ጋር መወያየታቸውን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ኦባሳንጆ “ጦርነት የፖለቲካዊ ውድቀት ነጸብራቅ ነው። ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ የለም። በጦር ሜዳ የሚገኝ ድል በኢትዮጵያ አስተማማኝ ፖለቲካዊ መረጋጋትን አያመጣም፤ ስለዚህም በውይይት ሰላም ለማምጣት ብቸኛው ዘላቂና አስተማማኝ መንገድ ነው” ብለዋል። ኦባሳንጆ በመግለጫው “ወታደራዊ ግጭት በሚካሄድበት ሁኔታ የሚደረግ ንግግር የሚጠበቀውን ውጤት ስለማያመጣ ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ ጥቃት በማቆም” ለውይይቱ መቀጠል እድል እንዲሰጡ ጥሪ አቀርበዋል።
በጦርነቱ ተሳታፊ ከሆኑት ወገኖች በተጨማሪም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መሪዎች የሽምግልና ጥረታቸውን መደገፋቸውን እንዲቀጥሉና “አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ግጭቱ እንዲባባስ ከሚያደርጉ እርምጃዎችና ንግግሮች እንዲቆጠቡ” ኦባሳንጆ ጠይቀዋል።
መፍትሄ ፍለጋ
አንድ ዓመት አስቆጥሮ በአሁኑ ወቅት በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ተባብሶ በመቀጠሉ የተለያዩ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ግፊት እያደረጉ ነው። በተለይ በአፍሪካ ሕብረት የተሰየሙት ኦሉሴጉን ኦባሰንጆ ከሁለት ሳምንት ወዲህ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር አዲስ አበባ እንዲሁም ከትግራይ መሪዎች ጋር ደግሞ መቀለ ላይ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን በተጨማሪም ከክልል ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
የኦባሰንጆ ጥረት በሁሉም ወገን ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ያደረጉት ጉዞ መሆኑንና አወንታዊ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸዋል። ለግጭቱ አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ እንዳለበትና ያለው ዕድልና ጊዜም ውስን መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አመለክተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱ ሰለማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የህወሓት ኃይሎች ከያዟቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች መውጣት እንዳለባቸው ገልጾ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
በህወሓት በኩልም ከዚህ በፊት የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ሲሆን፤ የኦባሳንጆ ጥረት የሚያስገኘው ውጤት በቀጣይ ቀናት የሚታይ ይሆናል። በጦርነቱ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ በትክክል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በሺዎች የሚቆጠር ሳይሆን እንደማይቀር በርካቶች ይገምታሉ። ከዚህ ባሻገርም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታን የሚሹ ሲሆን ከመካከላቸውም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ከሳምንታት በፊት ገልጾ ነበር።
ምንጭ – ቢቢሲ