የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት በሁለት ወራት ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በርካታ ሰዎች የአካል እንዲሁም የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው ይፋ አደረገ።

ከሐምሌ 2013 ዓ. ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ ማድረጉን ተከትሎ ነው ኮሚሽኑ ሪፖርት ያወጣው። “በተለይ የህወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር ባስገቧቸው ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውና ማቁሰላቸው፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሆን ብለው መፈጸማቸው ተረጋግጧል” ብሏል። ከሰኔ 21 እስከ ነሐሴ 22/2013 ዓ. ም. ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው ሪፖርት መሠረት፤ የህወሓት ኃይሎች ወደ ከተሞች ከባድ መሣሪያዎችን መተኮሳቸው ተገልጿል።

“በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈር እና ከባድ መሣሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአጸፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሣሪያዎች ጥቃት አጋልጠዋል” ሲል ሪፖርቱ ይጠቁማል። በዚህም የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞት እና አካል ጉዳት እንደተከሰተ፣ ንብረትም እንደወደመ ተገልጿል። ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን 128 ቃለ መጠይቆችን ከማድረጉ በተጨማሪ ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ጋር ተነጋግሯል። የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሲቪል እና የፀጥታ አካላት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ የተራድኦ ድርጅቶችን ጨምሮ 21 የቡድን ውይይቶችን እንዳደረገም አስታውቋል።

በዚህ ምርመራ መሠረት፤ የመከላከያ ሠራዊት የህወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈጽሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት ከባድ መሣሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና አካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረትም ወድሟል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው” ብለዋል።

አያይዘውም ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ሲቪል ሰዎችን ከጦርነቱ ሰለባነት የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩና የድርጊቶቹን ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ኮሚሽኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል። “ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ እራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲልም ምክረ ሐሳቡን አስቀምጧል።

በአማራ ክልል፣ በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በጦርነት የተጎዱ አካበቢዎች የመልሶ መቋቋሚያ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ኮሚሽኑ አክሏል። ህወሓት በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ከዚህ በፊት ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ተቋም ጋር በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ጥሰቶችን በመረመረበት ወቅት ህወሓት ኢሰመኮን ገለልተኛ አይደለም ሲል መተቸቱ ይታወሳል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተፋፋመበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሕብረት ለአፍሪካ ቀንድ የሾማቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ አካላት ለሰላማዊ ድርድር መንገድ እንዲከፈት እያሳሰቡ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት “ሰላም እንዲወርድ ህወሓት ከያዛቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች መውጣት አለበት” ብሏል። በተጨማሪም ህወሓት ለፌደራሉ መንግሥት ሕጋዊነት እውቅና መስጠት እና መቀበለ እንዳለበት እና ኃይሎቹ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ማቆም እንዳለበት ገልጿል።

በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት በበኩሉ “ትግራይ ላይ የተጣለው ከከባ እስከሚነሳ ድረስ በትግል እንደሚቀጥል” በተደጋጋሚ አስታውቋል። ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦትን ጨምሮ ስልክ፣ መብራት፣ ባንክ እና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስን በቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል። የአሜሪካ መንግሥት ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀድ አካሎች በበኩላቸው የፌደራል መንግሥቱም ይሁን ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲሄዱ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለውበታል።

ምንጭ – ቢቢሲ