በጂቡቲ የአሜሪካ ጦር አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ዊሊያም ዛና፤ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ለቀጠናው ስጋት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በአፍሪካ ግዙፉን የአሜሪካ የጦር ሰፈር የሚመሩት ጄነራል ዊሊያም፤ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግጭት በቀጠናው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራዋል ብለዋል። ጄነራሉ አያይዘውም “አዲስ አበባ በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር ብትወድቅ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ይከሰታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አዲስ አበባ በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ብትወድቅ የዚህ ጦር ቀጠና ተግባራት ምን ሊሆን ይችላል? ተብለው የተጠየቁት ጄነራል ዊሊያም፤ በጂቡቲ የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ቀጠና ዋነኛ ዓላማ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ በቀውስ ወቅት ምላሽ መስጠት መሆኑን መልሰዋል።

ጄነራሉ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞችን፣ አሜሪካውያንን እና የሌሎች አገራት ዜጎችን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝርዝር የሆነ ዕቅድ ማውጣታቸውን እና ዝግጅት ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የህወሓት አማጽያን የአማራ ክልል ከተሞቹን ደሴ እና ኮምቦልቻ እንደተቆጣጠሩ ከገለጹ በኋላ ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ጋር ተገናኝተው በጋራ መዋጋት እንደጀመሩና ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ እንደሚሄዱም አስታውቀዋል። ጦርነቱ እጅግ በተፋፋመበት በዚህ ወቅት የፌደራል መንግሥቱ በመላው አገሪቱ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

የአፍሪካ ሕብረት ለአፍሪካ ቀንድ የሾማቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ለሰላማዊ ድርድር መንገድ እንዲከፈት ለማስቻል ጥረት እያደረጉ ነው። በአፍሪካ ግዙፉን የአሜሪካ የጦር ሰፈር የሚመሩት ጄነራል ዊሊያም፤ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ጦርነት በቀጠናው ላይ አደጋ እንደሚያስከትል ስጋታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል። “ትልቁ ስጋቴ በኢትዮጵያ የሚከሰተው የትኛውም ነገር በቀጠናው ካሉ አገራት ደኅንነት እና መረጋጋት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው” ብለዋል የጦር መኮንኑ።

ጄነራሉ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በሚያጋጥማት ውስጣዊ አለመረጋጋት ጦሯን ከሶማሊያ ብታስወጣ አምስት የአፍሪካ ሕብረት አገራት በዚህ ውሳኔ ይጎዳሉ ሲሉ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ በሶማሊያ የተሠማራ ጦርን የማስወጣት ውሳኔ “ጽንፈኛ የሆኑ ቡድኖች እንቅስቃሴን [በሶማሊያ] እንዲጨምር ያደርጋል” የሚሉት ጄነራሉ፤ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ያለውን የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ እንዲሁም ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ውስብስብ እንደሚያደርገውም አመልክተዋል። ጄነራሉ የኢትዮጵያ አለመረጋገት ሥር እየሰደደ በሄደ ቁጥር ሱዳን እና ግብፅ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸውም ጨምረው ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር ያላትን የሕዳሴ ግድብ እና የድንበር ውዝግብ ድርድር ማስቀጠል የማትችልበት ሁኔታ ቢፈጠር፤ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ ትኩረት ስታደርግ ሌሎች አገራት ጠንካራ የሆነ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል በሚል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብዬ እሰጋለሁ” ይላሉ። በአንድ አገር ቀውስ ሲከሰት ሌሎች አገራት በዚያ አገር ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደ ሁነኛ አጋጣሚ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ የሚሉት ጄነራል ዊሊያም፤ መሰል እርምጃ በሱዳን እና በግብፅ የሚወሰድ ከሆነ በአገራቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሻከረ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ