ባለፈው ሳምንት በመላው አገሪቱ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን የሚከታተለው ዕዝ አስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በመመርመር ተጨማሪ ሦስት ትዕዛዞችን አስተላለፈ።

አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን አገራዊ ሁኔታና የአዋጁን አፈጻጸም ትናንት ረቡዕ ገምግሞ ዕዙ ባወጣው መግለጫ ላይ ሕዝቡ ለቀረበለት ጥሪ የሰጠውን ምላሽ፣ ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ውጊያዎች ተመዘገቡ ያላቸውን ውጤቶች ገልጾ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ እርምጃዎችን አሳውቋል። በዚህም መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ “ሕገወጥ ግለሰቦችንና በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን መያዙን” ገልጾ፣ በዚህም “ጠላት የፀጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” ብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የፀጥታ አካላት መኖራቸውን ዕዙ እንደደረሰበት እና “በእነዚህም ላይ በመረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ” ትዕዛዝ መሰጠቱን ገልጿል። በተጨማሪም “ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር እንዲያግዝ” ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ በአንድ ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲያስመዘገብ በማዘዝ፣ ይህን በማይፈጽሙ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

“ሕገወጥ ግለሰቦች” ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው ደንቦችና የአፈጻጸም መመሪያዎችና ከባንኮች ሕጋዊ አሠራር ውጪ በተጭበረበረ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እያካሄዱ መሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚው ዕዝ እንደደረሰበት እና ተገቢው እርምጃ መወሰዱን ገልጿል። ስለዚህም ቀደም ብለው ከወጡ ሕጎችና መመሪዎች ውጪ ሲሠሩ በሚገኙ ባንኮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ ታዟል።

በተጨማሪም ማንኛውም የተጭበረበረ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሰነድ ይዘው በተገኙ ግለሰቦች ላይ “ከወትሮው በተለየ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ”ትዕዛዝ መተላለፉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚከታተለው ዕዝ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ዕዙ ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ ካስተላለፈቸው ትዕዛዞች በተጨማሪ ባለፉት ቀናት ጦርነት እየተካሄደባቸው ባሉ አካባቢዎች ተገኝተዋል ያላቸውን ውጤቶች በዝርዝር አስፍሯል።

መግለጫው ባለፉት ቀናት በባቲ- አሳጊታ ግንባር፣ በትግራይና አፋር ክልል ወሰን ላይ ቢሶበር አካባቢ፣ በወረኢሉ ግንባር፣ በአቀስታ ግንባር፣ በከሚሴ ግንባር እና በማይጸብሪ ግንባር በተለያዩ ደረጃዎች ውጊያዎች መደረጋቸውን አመልክቷል። የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት እና አየር ኃይል በተጨማሪ የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ተሳትፈውበታል በተባሉትና በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ በተካሄዱት እነዚህ ውጊያዎች የተገኘው ውጤት “አመርቂ ውጤት” ነው ብሏል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮጉድሩ እና በምሥራቅ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የፌዴራል ፖሊስና የአገር መከላከያ በጋራ በወሰዱት እርምጃ የሸኔ’ ቡድን አባላት “መደምሰሳቸውንና በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን” ገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ” ይህንንም አደጋ “በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ” ታስቦ እንደታወጀ መገለጹ ይታወሳል።

ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደንግጎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት የሚቆይ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚከታተለውና የሚያስፈጽመው ‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ’ የተባለ አካል ሲሆን ይህ የተለያዩ አካላትን የተካተቱበት ዕዝ በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሚመራና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *