የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 72 የዓለም ምግብ ፕሮግራም የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች አፋር ክልል ሰመራ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሮይተስና እና ኤኤፍፒ ዘገቡ።

“በዓለም ምግብ ድርጅት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ 72 አሸከርካሪዎች ሰመራ ከተማ ላይ መታሰራቸውን እናረጋግጣለን። ሠራተኞቹ ለምን እንደታሰሩ ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” በማለት የድርጅቱ ቃልአባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ይህ የዓለም ምግብ ድርጅት አሸከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር የመዋል ዜና የተሰማው፤ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ቢያንስ 16 የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

ተመድ ትናንት አመሻሽ ላይ ቢያንስ 16 የሚሆኑ ሠራተኞቹ እና ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸውን ካስታወቀ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ተፈጸመ የተባለው “የዓለም አቀፍ ድርጅቱ ሠራተኞች እስር አሳስቦኛል” ብሏል። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የተመድ ሠራተኞች እስር አሜሪካን “አስሰቧል” ካሉ በኋላ፤ “ማንነትን መሠረት ያደረጉ እስሮች በፍጹም ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ መንግሥት በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሏል ሲል ዘግቦ ነበር። የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ የአሸከርካሪዎቹን መታሰር ባስታወቁበት ወቅት፤ “ደኅንነታቸውን እንዲያረጋግጥ ሰብዓዊ እና ሕጋዊ መብታቸው እንዲከበር እየጠየቅን ነው” ብለዋል።

ሮይተርስ በዘገባው በሰመራ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አሸከርካሪዎች ብሔር እስካሁን ግልጽ ባይሆንም፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ እርዳታዎችን ወደ ትግራይ እንዲያጓጉዙ የትግራይ ተወላጆችን ቀጥሮ ነበር ብሏል። የመንግሥታቱ ድርጅት ታሰሩብኝ ስላላቸው ሠራተኞቹ ጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የሰጠው ማብራሪያ የለም።

የፌደራሉ መንግሥት ከአንድ ወር በፊት “የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል” ያላቸውን ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ማባረሩ ይታወሳል። ይህ የመንግሥት ውሳኔን ተከትሎም ምዕራባውያን አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተው ውሳኔው እንዲቀለነበስ በተደጋጋሚ ጠይቀው ነበር። መንግሥት በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ለህወሓት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ ሲል ክስ ሲያቀረብ ቆይቷል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *