የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢያንስ አስራ ስድስት ሠራተኞቹ እና የቤተሰብ አባሎቻቸው አዲስ አበባ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገለጸ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደኅንነት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉትን የድርጅቱን ሠራተኞች ጎብኝተዋል። የፈረንሳይ ዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) በበኩሉ የተመድ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋሉት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ናቸው።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ መንግሥት በርካታ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሏል ሲል ዘግቧል። የዜና ወኪሉ ጨምሮም አንድ ምንጭ “አንዳንዶቹ ከመኖሪያ ቤታቸው ነው ተይዘው የተወሰዱት” ሲሉ ተናግረዋል ብሏል።

ተመድ ሠራተኞቹ መታሰራቸውን ካስታወቀ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት የተመድ ሰራተኞች እስር አሳስቦኛል ብሏል። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የተመድ ሰራተኞች እስር አሜሪካን “አስሰቧል” ካሉ በኋላ፤ ማንነትን መሠረት ያደረጉ እስሮች በፍጹም ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል። “ሪፖርቶች እስሮቹ የተፈጸሙት ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ እንደሆነ ይጠቁማል። ይህ ከተረጋገጠ አጥብቀን እናወግዛለን። እነዚህን ግለሰቦች ለማስፈታት የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንሆናለን” ብለዋል ኔድ ፕራይስ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በፀጥታ ኃይሎች ተይዘዋል የተባሉትን ሠራተኞቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንደጠየቀ ሮይተርስ የድርጅቱን ቃል አቀባይን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። በጉዳዩ ላይ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም። ሮይተርስ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉን አስተያየት ለማካተት ያደረኩት ጥረት አልተሳካም ብሏል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፋሲካ ፈንታ በበኩላቸው እስሩን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

መንግሥት ከአንድ ወር በፊት “የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል” ያላቸውን ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ማባረሩ ይታወሳል። ይህ የመንግሥት ውሳኔን ተከትሎም ምዕራባውያን አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተው ውሳኔው እንዲቀለነበስ በተደጋጋሚ ጠይቀው ነበር። መንግሥት በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ለህወሓት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ ሲል ክስ ሲያቀረብ ቆይቷል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *