ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የነፋስ መውጫ ከተማ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ የአስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ እና አካላዊ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።

የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በከተማዋ ነዋሪ የሆኑና ያናገራቸው 16 ሴቶች በህወሓት አማጺያን የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ሴቶቹ እንዳሉት በህወሓት ኃይሎች መሳሪያ ተደቅኖባቸው እንደተደፈሩ፣ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው እንዲሁም አካላዊ ጥቃት እና ስድብ እንደደረሰባቸው አመልክተዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽ ጨምሮ ካነገራቸው አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ከተፈጸመባቸው አስራ ስድስት ሴቶች መካከል 14ቱ ጥቃቱ በቡድን እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል። አማጺያኑ በከተማ ባሉ የህክምና ተቋማት ላይ ዝርፊያና ውድመትን አድርሰዋል ብሏል።

ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ የህወሓት አማጺያን ወደተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመግባት ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ ነበር ወደ ንፋስ መውጫ ከተማ የገቡት። በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የምትገኘውን የነፋስ መውጫ ከተማን የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረው የቆዩት ከነሐሴ 06 አስከ 15/2013 ዓ.ም ድረስ ለአስር ቀናት ነበር። አንድ የክልሉ አስተዳደር ባለሥልጣን ለአምነስቲ እንደገለጹት አማጺያኑ በንፋስ መውጫ ከተማ በቆዩባቸው ቀናት ውስጥ ከ70 በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሪፖርት አድርገዋል።

“የአስገድዶ መድፈር ጥቃቱ ከደረሰባቸው የሰማናቸው ምስክርነቶች የህወሓት ተዋጊዎችን አጸያፊ ተግባራት፤ ከጦር ወንጀሎች እና በሰብአዓዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ናቸው። ድርጊቶቹ ከሞራል ወይም ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ናቸው” ሲሉ የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ ተናግረዋል። ጨምረውም የህወሓት ተዋጊዎች ወሲባዊ እና ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕጎች ጥሰቶችን በሙሉ በማቆም በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

አምነስቲ ያናገራቸው የአካባቢው የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሠራተኛ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 71 ሴቶች በህወሓት ተዋጊዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራል ፍትህ ሚኒስቴር አሃዙ 73 እንደሆነ ያመለክታል። ከጥቃቱ የተረፉ ሴቶች ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት እንደተናገሩት ጥቃቱን መፈጸም የተጀመረው የህወሓት ኃይሎች ከተማዋን በተቆጣጠሩበት ዕለት ነው። ሁሉም ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ፈጻሚዎቹን ህወሓቶች መሆናቸውን መለየት የቻሉት በአነጋገር ዘያቸው እና በሚሰነዝሩት ብሔርን መሠረት ባደረገ ስድብ እንዲሁም በግልጽ ህወሓቶች መሆናቸውን በመናገራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አማጺያኑ ከአስገድዶ መድፈሩ በተጨማሪ ሰብዓዊነትን የሚያጣጥል የብሔር ማንነታቸው ላይ ያነጣጠሩ ስድቦችንና ማዋረድን ይፈጽሙ ነበር። እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ አስገድደው የሚደፍሩት በፌደራል ኃይሎች በትግራይ ሴቶች ላይ የተፈጸመውን ተመሳሳይ ድርጊት ለመበቀል መሆኑን ይናገሩ ነበር ብለዋል። አምነስቲ ኢንትርናሽናል እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት ቀደም ሲል የመንግሥት አጋር በሆኑ ኃይሎች እና በሚሊሻዎች ትግራይ ውስጥ ስለተፈጸሙት መጠነ ሰፊ የአስገድዶ መድፈር እና ፆታዊ ጥቃት መረጃዎችን ማውጣታቸው ይታወሳል።

የህወሓት ታጣቂዎች በነፋስ መውጫ በቆዩባቸው ቀናት ከፈጽሟቸው አስገድዶ መድፈር፣ አዋራጅ ንግግር እና አካላዊ ጥቃቶች በተጨማሪ ዘረፋና ንብረታቸው ላይ ውድመትን መፈጸማቸውን የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል። አስገድዶ መድፈር የተፈጸመባቸው ሴቶች በህወሓት ኃይሎች የተለያዩ ንብረቶቻቸው እንደተወሰዱባቸው ለአምነስቲ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ምግብ፣ ጌጣጌጦች፣ ገንዘብና የሞባይል ስልኮች እንደተወሰደባቸው አመልክተዋል። የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ያነጋገራቸው 16 የአስገድዶ መድፈር ሰለባዎች በጥቃቱ ሳቢያ የተለያዩ አካላዊና አእምሯዊ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል። በአካባቢው ያሉ የህክምና ተቋማት በአማጺያኑ በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ሴቶቹ የህክምና ድጋፍ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው አምነስቲ ገልጿል።

በመንግሥት በአሸባሪ ቡድንነት የተፈረጀው ህወሓት አምነስቲ ኢንትርናሽናል ተዋጊዎቹ ፈጽመውታል ስላላቸው የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች፣ ዘረፋ እንዲሁም ሌሎች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን በመተመለከተ አስካሁን ያለው ነገር የለም። የፌደራሉ መንግሥት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ አካባቢዎች ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች በአጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ጥቃት ከፍተው የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ይታወሳል። በዚህ ሳቢያም የህወሓት አማጺያን የጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ እና ሌሎች ጥፋቶችን እየፈጸሙ ነው በሚል በተደጋጋሚ ቢከሰሱም ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *