የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የፌደራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማደራደር የሚያደርጉትን ጥረት ‘አልቀበልም’ ያለ ወገን እንደሌለ ለቢቢሲ ገለጹ።
ወደ ትግራይ መዲና መቀለ ሄደው ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገው የተመለሱት ልዩ መልዕክተኛው፤ “ለማደራደር የማደርገውን ጥረት ‘አልቀበልም’ ያለ የለም” ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ለማሸማገል እየሞከሩ ካሉት የፌደራል መንግሥት ወይም የህወሓት አመራሮች ዘንድ ሸምግልናውን አልቀበልም ያለ ወገን አለ? ተብለው የተጠየቁት ኦባሳንጆ፤ “የአፍሪካ ሕብረት ሰላም ለማምጣት፣ ንግግርን ለማስጀመር እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ልዩ መልዕክተኛ መሰየሙን ሁሉም ወገን በበጎ ነው የተቀበሉት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ “የጠየቅኩትን ትኩረት ሰጥተውኛል። በሚገባው ልክ አስተናግደውኛል” ሲሉ ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ገልጸዋል። አያይዘውም “ትግራይ ስገባም የትግራይ ፕሬዝዳንት አየር ማረፊያው ድረስ መጥተው ተቀብለውኛል። ሌላ የአፍሪካ መሪ በሚቀበለኝ ክብር ነው የተቀበሉኝ” ብለዋል። ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛው ኦባሳንጆን “አልተቀበሉንም የሚለው ሐሳብ ፍጹም ስህተት ነው” ሲሉም አክለዋል።
ድርድሩ ምን ላይ እንዳለና በቀጣይ ምን እንደሚፈጠር ጥያቄ የቀረበላቸው ኦባሳንጆ “አሁን ገና የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነኝ። ድርድሩ ወዴት እንደሚሄድ የምናገርበት ጊዜ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አሁን ያሉበት ደረጃ በተደራዳሪ ወገኖች ዘንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ምን እንደሆነ የመለየት እንደሆነም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኦባሳንጆ “ይዘው የሚመጡትን መፍትሔ እየጠበቅኩ ነው” ሲል ገልጿል። የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ የአፍሪካ ቀንድ ልዑኩ “ከትግራይ ፕሬዝዳንት ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል። በወቅታዊው የኢትዮጵያ ቀውስ ዙርያ የትግራይ አቋም ምን እንደሆነ ገልጸውላቸዋል” ሲሉ በይፋዊ ትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ኦባሳንጆ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሁለቱም ወገን በኩል የእሳቸው የማደራደር ጥረት ተቀባይነት አግኝቷል። “ማንም የእኔን የማደራደር ሐሳብ ውድቅ አላደረገም። ሁሉም ያሉት እርስዎ ለማደራደር መመረጥዎን እናከብራለን ነው። እንደ እርስዎ ሐቀኛ አሸማጋይ ስንፈልግ ነው የነበረው። ከእርስዎ የተሻለ አሸማጋይ አናገኝም ብለዋል” ሲሉም ተናግረዋል። የአፍሪካ ሕብረት ኦባሳንጆን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ሲሾም የመጀመሪያ ጉዳያቸው አድርገው የወሰዱት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ነው።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በአፍሪካ ቀንድ እና ከአፍሪካ ቀንድ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላትንም ማማከር ነው። ከዚያም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላትን እንዳገኙ ጠቅሰው፤ “ሁሉም የሚያሳስባቸውን ነገር እንዲሁም ፍላጎታቸውን ገልጸዋል” ሲሉ አሁን የሚገኙበትን ደረጃ ገልጸዋል። የሰሜኑ ጦርነት በተለይም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እጅግ እየተባባሰ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ሁለት ቀናት መቆየታቸው ይታወሳል።
ከኦባሳንጆ በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስም ወደ ተጉዘው እንደነበር ተገልጿል። በፌደራል መንግሥቱ እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የተፋፋመውን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለ12ኛ ጊዜ ውይይት አድርጓል። ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ከወራት በፊት ወደ አማራና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በድርድር መፍትሄ እንዲፈለግለት የተለያዩ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታይ እንደቀጠለ ይገኛል። በዚህ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገምታሉ። የተባሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።