የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ትናንት እሁድ ወደ መቀለ ተጉዘው እንደነበረ ተነገረ።

ትናንት እሁድ ጥቅምት 28/2014 ዓ.ም. ወደ ትግራይ መጓዛቸው የተገለጸው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ናቸው። ሁለቱ የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች ወደ መቀለ ስለማቅናታቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን የተለያዩ ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ቢዘግብም ከድርጅቶቹ ቀጥተኛ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ አመልክቷል።

በተጨማሪም የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ “ሁለቱ ባለሥልጣናት እዚህ [መቀለ] መሆናቸውንና ውይይት እያካሄድን መሆኑን ማረጋገጥ እችላለሁ” በማለት ለዜና ወኪሉ ያረጋገጡ ሲሆን ትናንት ምሽት ሁለቱ መሪዎች ከህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

“ውጤታማ ውይይት”

አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ ኦባሳንጆ እና ማርቲን ግሪፊትስ ከደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር መገናኘታቸውን አረጋግጠው፤ “ውይይቱ ውጤታማ ነበር” ብለዋል። አቶ ጌታቸው፤ ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የትግራይን አቋም ለሁለቱ ባለስልጣናት ገለጻ አድርገዋል ከማለት ውጪ መልዕክተኞቹ ከደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ጋር በምን ጉዳይ እንደተወያዩ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ትናንት ማምሻውን የትግራይ ቴሌቪዥን ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ማርቲን ግሪፊትስ ከደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው “በኢትዮጵያ ባለው ፖለቲካዊ ቀውስና በሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች” ላይ ተወያይቷል ሲል ዘግቧል። ጨምሮም ኦባሳንጆና ግሪፊትዝ በመቀለ የነበራቸውን ቆይታ በአንድ ቀን ውስጥ አጠናቀው እሁድ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ገልጿል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት ከጥቂት ወራት በፊት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ በልዩ መልዕክተኝነት መሰየሙ ይታወሳል። የልዩ መልዕክተኛው ጉዞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊነትን የተረከቡት ማርቲን ግሪፊትስ በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ ወደ ክልሉ ሲያቀኑ ይህ ሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በሐምሌ ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር።

ሁለቱ ባለሥልጣናት እሁድ ዕለት መቀለ ባደረጉት ውይይት ላይ ስለተነሱ ጉዳዮችና ስለተገኙ ውጤቶች አስካሁን በግላቸውም ሆነ በተቋማቸው በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ከወራት በፊት የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በድርድር መፍትሄ እንዲፈለግለት የተለያዩ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታይ እንደቀጠለ ይገኛል። በዚህ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገምታሉ።

የተባሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።

 

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *