የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ተከትሎ የሚፈጸሙ እስሮች ብሔርን መሠረት ባደረገ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ አሳስቦኛል አለ።

ኢሰመኮ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ በተለይም በአዲስ አበባ “ማንነትን/ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ እጅግ ያሳስበኛል” ብሏል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ያወጀው “በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ” እንደሆነና ይህንንም አደጋ “በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ” ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስፈለጉ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል።

የአስቸኳይ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራእ ተወላጆች “ትግራዋይ ከሆንክ ምንም አይነት ተስፋ የለህም። ትታሰራለህ። እስሩም የሚደረገው በብሔር ስም ነው” ብለው ነበር። በአዲስ አበባ የምትኖር ሌላ የትግራይ ተወላጅ እና የሕግ ባለሙያ ደግሞ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ “የተወለድኩባት እና ያደኩባት ከተማ” አይደለችም ስትል የጅምላ እስሩ የፈጠረባትን ስሜት ለቢቢሲ አጋርታለች።

በመዲናዋ አዲስ አበባ የህወሓት አማፂኣን ደሴንና ኮምቦልቻን መቆጣጠራቸው ከተገለፀ ወዲህ የብሔረ ውትረት መጨመሩን ቢቢሲ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መረዳት ችሏል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው እስር የሚፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚያሳይ ማስረጃ ከተገኘ በኋላ ነው ብለው ነበር። ቃለ አቀባዩ የታሰሩት አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ቢያረጋግጡም የሌላ ብሔር ተወላጆችም መታሰራቸውን ተናግረዋል።

ኢሰመኮ በበኩሉ በተለያዩ ከተሞች የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ ክትትል ማደረጉን ገልጾ፣ ሰዎች እየታሰሩ እንዲሁም ከታሰሩ በኋላ የሚቆዩበት የአያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም ገልጿል። “የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ሰዎች ከስራ ቦታቸው፣ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም ከመንገድ ላይ ጭምር ተይዘው በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሚገኙ” ተረጋግጧል ይላል መግለጫው።

ኢሰመኮ በመግለጫው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ለጸጥታ ኃይሎች ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራሉ ብሎ በበቂ ምክንያት የጠረጠራቸውን ሰዎች የመያዝ ስልጣን ቢሰጠውም፤ ይህ እየተፈጸመበት ያለው አግባብ ግን እንደሚያሳስበው ገልጿል። እንዲሁም በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች ምግብ እና ልብስን ጨምሮ መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ለታሰሩ ሰዎች ለማቀበል ብሎም የታሰሩ የቤተሰብ አባላትን ለመጠየቅ አለመቻሉን መታዘቡን ኮሚሽኑ ገልጿል። በእስር ላይም ህጻናት ልጆች ያሏቸውን እናቶችን ብሎም አዛውንቶችን ማካተቱ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል ሲልም የሰብአዊ መብት ተቋሙ ገልጿል።

የሕግ አስከባሪ አካላት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በሚያስፈጽሙበት ወቅት መሠረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን እንዲተገብሩ ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል። እነዚህ የሕግ አስከባሪዎች በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅትም ሊገደቡ የማይችሉ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ ተግባራቸውንም በከፍተኛ የሙያ ስነ ምግባር ሊያካሂዱ እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳስቧል። አረጋዊያንን፣ የህጻናት ልጆች እናቶችን፣ የሕክምና ክትትል የሚፈልጉ ሰዎችን እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በተመለከተ ፈጣን እና ልዩ የማጣራት ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል ሲልም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *