በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በመስቀል አደባባይ ተገኝተው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከአማጺያን ጋር በሚደረገው ጦርነት ለመንግሥት ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ።

ዛሬ እሁድ ጥቅምት 28/2014 ዓ.ም ከማለዳው ጀምረው በከተማዋ ዋነኛ አደባባይ የተሰበሰቡት የከተማዋ ነዋሪዎች አንድ ዓመት በሆነው ጦርነት ውስጥ ለሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥትና ለአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። በዚህ ሰልፍ ላይ ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የመጡ ነዋሪዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎችም ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር ለሰልፍ የወጣውን ታዳሚ ለአገሪቱ ሠራዊት ድጋፋቸውን በመግለጻቸው “ለኢትዮጵያ ጥሪ በአንድነትና በፍፁም ኢትዮጵያዊነት ለሰጣችሁት ከፍተኛ የአገር ፍቅርና ወኔ የታየበት ምላሽ እጅጉን የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል። የከተማዋ ባለሥልጣንት ይህንን ሰልፍ ያጋጁት በመንግሥትና በአማጺያኑ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት በቀጠለበትና ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ዓለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደውን አይነት ተመሳሳይ ሰልፎች ባለፉት ቀናት በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ የተካሄዱ ሲሆን ሰልፈኞቹ መንግሥት የሚያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚደግፉና ዓለም አቀፍ ግፊትን የሚቃወሙ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ወጥተዋል። አማጺያኑ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቀው የሚገኙትን በአማራ ክልል ያሉትን ከተሞች ደሴን እና ኮምቦልቻን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ መዲናዋ ማቅናታቸውን እንደሚቀጥሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ነዋሪዎች በእጃቸው የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም በአካቢያቸው ያሉ እንቅስቃሴዎችን በንቃት እንዲከታተሉና ለፀጥታ አካላት እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል። በትግራይ ክልል ውስጥ ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ ደግሞ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እንደቀጠለ ይገኛል።

አሜሪካ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አስቸኳይ የተኩስ አቁም ተደርጎ በመንግሥትና በአማጺያኑ መካከል ድርድር እንዲጀምር በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም አስካሁን ውጤት አላስገኘም። ከቀናት በፊት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣንት ጋር መነጋገራቸው የተገለጸው የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ስለደረሱበት ውጤት እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።

በዚህ አንድ ዓመት በሞላው ጦርነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን፣ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ የእርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *