የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ጦርነት አስቸኳይ መፍትሔ ለማፈላግ አዲስ አበባ ውስጥ ለሁለት ቀናት እንደሚቆዩ ተነግሯል።

ፌልትማን በዚህ ቆይታቸው ከአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት፣ ከሕብረቱ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል። ጄፍሪ ፌልትማን በፕሬዝዳንት ባይደን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በሱዳን ሁለት ዓመት በሞላው ፖለቲካዊ ቀውስና አንደኛ ዓመቱን በደፈነው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝ ለማገዝ ወደ አፍሪካ ቀንድና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተደጋጋሚ ተመላልሰዋል።

የሱዳኑ ቀውስ ወደ መፈንቅለ መንግሥት ተሸጋግሮ ችግሩ የተባባሰ ሲሆን በኢትዮጵያም ያለው ጦርነት ሳያበቃ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ ይገኛል። ፌልትማን በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ሰላማዊ መቋጫ ያገኝ ዘንድ ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በእርሳቸውና በአሜሪካ መንግሥት ላይ የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘሩባቸው ቆይተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን ስለጦርነቱና ስለሚሰነዘሩባቸው ትችቶች እንዲሁም በኢትዮጵያ ዙሪያ ያላቸውን ምልከታ በስፋት በጽሑፍ አጋርተው ነበር። አምባሳደሩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገጽ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የመንግሥታቸውን አቋምም አንጸባርቀዋል።

‘ኢትዮጵያ ን ስላለችበት ሁኔታ

አምባሳደር ፌልትማን በተባበሩት መንግሥታት በነበራቸው ረዥም ቆይታቸው የምሥራቅ አፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችን በቅርበት ተከታትለዋል። ፌልትማን በጽሑፋቸው እአአ 2015 ላይ በ2021 የአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ጉዳይ ምን ሊሆን ይችላል ተብዬ ብጠየቅ በቀዳሚነት የማስቀምጠው፤ ሶማሊያን ነበር ይላሉ።

ሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ቀጠና የምታረጋጋዋ እና የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ 2021 በዋይት ሐውስ ዋና መወያያ አጀንዳዬ ትሆናለች ብዬ በጭራሻ አልገምትም ነበር ይላሉ።

‘አሜሪካ ለህወሓት ታደላለች’

ፌልትማን በጽሑፋቸው አብዝቶ ከሚደርሷቸው ትችቶች መካከል አንዱ ‘የአሜሪካ መንግሥት እና እርሳቸው ለህወሓት ወገንተኛ ናችሁ’ የሚለው አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ። ፌልትማን በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተመድን ወክለው ያደረጉት ንግግር ከዓመታት በኋላ የህወሓት ደጋፊ ናቸው እንዳስባለቸው ይገልጻሉ። ፌልትማን በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን፤ “አስደናቂ መሪ፣ በሰላም እና ልማት ፈተናዎች ተመድን በብዙ የረዱ” ሲሉ ገልጸዋቸው ነበር።

በአካል ባላገኘሁት ሰው ቀብር ላይ ተገኝቼ ያደረኩት ንግግር ከዓመታት በኋላ ለማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሐሰተኛ የዜና ግብዓት ይሆናል ብዬ አልጠበቀኩትም ብለዋል ፌልትማን በጽሑፋቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብታዊ የለውጥ እርምጃዎችን ማካሄዳቸውን አስታውሰው፤ በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት ለረዥም ዓመታት የዲሞክራሲ እና የአስተዳደር ድጋፍን አሻፈረኝ ብሎ ቆይቶ የአገሪቱን ሲቪል ማኅበራትን ለማንቃት የአሜሪካ ድጋፍን መቀበላቸውን ይጠቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን እንደመጡ የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት መጠናክሩን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የደረሰችው ስምምነት አሜሪካ ከአሥመራ ጋር ያላትን ግንኙነት የምታሻሽልበት እድል ይፈጥራል ብላ ዋሽንግተን ተስፋ አድርጋ እንደነበረ ፌልትማን ጽፈዋል።

“የእኛ ፍላጎት ይህ ነበር። አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ኤርትራ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳላት አሜሪካ ድጋፍ አድርጋ ነበር። አለመታደል ሆኖ ኤርትራ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጠችም፤ በቀጠናው አፍራሽ የሆነ ሚና እየተጫወተች ነው” ይላሉ። ይሁን እንጂ ይላሉ ፌልትማን፤ ከአውሮፓውያኑ 2020 በኋላ በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነት ንፋስ ይገባው ጀመረ።

የትግራይ ጦርነት

ፌልትማን የአሜሪካ መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለአገሪቱ አለመረጋጋት ትልቅ ስጋት መሆኑን ያምናል ይላሉ። የባይደን-ሃሪስ አስተዳደር በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭት አቁመው ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡንም ያስታውሳሉ። ከሰኔ ወር ማብቂያ ጀምሮ የትግራዩ ጦርነት የኃይል ሚዛን መቀየሩን ፌልትማን ጽፈዋል። “የህወሓት ኃይሎች የትግራይ መዲና መቀለን ሲቆጣጠሩ ጉልህ የሆነ የኃይል ሚዛን ለውጥ ተከስቷል” ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ህወሓት ጦርነቱን ወደ አጎራባች ክልል ማስፋፋቱ በእጅጉ አሳስቧታል ያሉ ሲሆን፤ የባይደን-ሃሪስ አስተዳደር ፖሊሲ ለህወሓት ያደላ ነው የሚለው አስተሳሰብ ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ። “በተደጋጋሚ የህወሓትን መስፋፋት አውግዘናል፤ ህወሓት ከአፋር እና አማራ ክልሎች ለቆ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባችንን እንቀጥላለን።” ፌልትማን በትግራዩ ጦርነት የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ሰዎች የሰብዓዊ አቅርቦት እንዳይደርስ በኢትዮጵያ መንግሥት እክል እንደሆነ ያብራራሉ።

ፌልትማን የሶሪያ መንግሥት በ10 ዓመታት ጦርነት ውስጥ ያላደረገውን የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ቀን በርካታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችን አባሯል ሲሉ ይወቅሳሉ። “ምግብ፣ ነዳጅ እና ተሸከርካሪዎች ለህወሓት የጦር አገልግሎት ሊውሉ ይችላሉ የሚለውን መከራከሪያ አውቃለሁ” ያሉት ፌልትማን፤ “ባለኝ ተሞክሮ ግን ለዚህ መሰል ስጋት አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ይቻላል” ይላሉ።

ለዚህም የእስራኤል እና የሳዑዲ አረቢያ ተሞክሮን አጋርተዋል። እስራኤላውያን በጋዛ ሰርጥ እንዲሁም ሳዑዲ መነሻቸው ከየመን የሆኑ የፀጥታ ስጋቶች እያሉባቸው ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚውሉ አቅርቦቶችን እንዴት ለሚገባቸው ማድረስ እንደቻሉ ዋቢ ይጠቅሳሉ። አሜሪካ፣ ተመድ እና በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእርዳታ አቅርቦቶች ወደማይፈለግ አካል አለመዘዋወራቸውን የሚያረጋግጥ አስገዳጅ ሥርዓት ይከተላሉ ይላሉ።

‘ግንኙነታችን እንደተለመደው አይቀጥልም’

“ወታደራዊ ግጭቱ እየተስፋፋ የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት እንደተለመደው አይቀጥልም። በአፍሪካ በርካታ ሕዝብ ካላቸው ቀዳሚ አገራት አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ፤ ጦርነት እየተስፋፋ፣ የአገሪቱን ደኅንነት እና አንድነት አደጋ ውስጥ ወድቆ አሜሪካ የተለመደው አይነት ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት አይችም” ይላሉ ፌልትማን። ለዚህም ማሳያ የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ መቀነሱን እንዲሁም በጦርነቱ ተሳታፊ ናቸው በተባሉ አካላት ላይ የባይደን አስተዳደር ያስተላለፈውን ውሳኔ ያወሳሉ።

ፌልትማን መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ግልጽ የሆነ ንግግር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉን ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ በአሜሪካ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በርካታ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በሐሰት ዋሽንግተን የህወሓት የበላይነትን ዳግም ለማምጣት ዐብይን በሌላ የመተካት ፍላጎት አላት ይላሉ ሲሉ ጽፈዋል። “ይህ እውነት አይደለም” የሚሉት ፌልትማን፤ የመለስ ዜናዊ አይነት አስተዳደር ተመልሶ በኢትዮጵያ እንዳይሰፍን “የአብዛኛው የኢትዮጵያዊ ፍላጎት መሆኑን እናውቃለን” ብለዋል።

“ይህ 1983 አይደለም። ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው ህወሓት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አልያም አዲስ አበባን ለመክበብ የሚያደርገውን ጥረት እንቃወማለን። ይህንም መልዕክት ለህወሓት አመራሮች ግልጽ አድርገናል።” ፌልትማን ምንም እንኳ በርካታ የፖለቲካ መሪዎች ታስረው በተከናወነ ምርጫም ቢሆን፤ ከወራት በፊት የተካሄው ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና ፓርቲ በመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ድጋፍ እንዳለው አሳይቷል ይላሉ።

ለሙሉ የስልጣን ዘመን የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ሰላም ለማስፈን እድል ቢኖራቸውም ይህን ግን ሊሆን አልቻለም ይላሉ። “ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሆነ እየተመለከትን ነው።” “ለልማት መዋል የነበረበት የውጭ ምንዛሪ ለጦር መሳሪያ ግዢ እና ሎቢ ለሚያደርጉ ወጪ እየሆነ ነው። ህወሓት በበኩሉ፤ በአማራ ወደፊት እየገፋ ከተገንጣይ ታጣቂ ቡድን ጋር አጋርነት ይፈጥራል። በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው የበለጠ አሳሳቢ ሆኗል።”

“ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት የእርስ በእስር ጦርነት በአማካይ 20 ዓመታት ሊዘልቁ ይችላሉ። እደግመዋለሁ 20 ዓመታት። ለሁለት አስርት ዓመት የሚዘልቅ የእስር በእስር ጦርነት ለኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ከፍተኛ አደጋ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም እድል እንዲሰጥ እናሳስባለን. . . ህወሓት ድርድር መምረጥ አለበት።”

ፌልትማን በጽሑፋቸው ማጠቃለያ ላይ፤ ጦርነቱን ማቆም የበለጸገች እና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁነኛው አማራጭ ነው ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ጦርነቱን ማቆም አሜሪካ እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ወዳጅነታቸውን እንደ አዲስ ለማደስ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

ሕዳሴ ግድብ

የባይደን-ሃሪስ አስተዳደር ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ትርጉም ያለው ድርድር አድርገው በግድቡ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ አስቸኳይ ስምምነት ማድረግ እንዳለባቸው ፍላጎት እንዳለው ይገልጻሉ። “የግብፅ የውሃ ደኅንነት፣ የሱዳን የደኅንነት ስጋት እና የኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት በመልካም እሳቤ ላይ የተመሠረተ ድርድር ተካሂዶ የሦስቱንም አገራት ፍላጎት ሊያስጠብቅ የሚችል ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል እምነት አሜሪካ አላት” ይላሉ።