የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ውይይት እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡን አየርላንድ ገለጸች።
የምክር ቤቱ አባል ሆኑት አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዚያ፣ ሴንት ቪንሰንት እና ዘ ግሪናዲስ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲመክር ስበሰባ እንዲካሄድ መጥራታቸው የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል የሆነችው አየርላንድ አስታውቃለች። የፀጥታው ምክር ቤት አሁን የተጠራውን ስብሰባ የሚያካሂድ ከሆነ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲመክር ለ11ኛ ጊዜ ይሆናል።
በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው አየርላንድ በኢትዮጵያ “በቅርብ ቀናት እየተባባሰ የመጣው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው” ካለች በኋላ፤ የተኩስ አቁም ድርድር ተካሂዶ ግጭት መቆም አለበት ብላለች። ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመክረው የህወሓት አማጺያን የሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ተቆጣጠረው፤ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባን የመያዝ ፍላጎት እንዳላቸው በገለጹበት ወቅት ነው።
ምክር ቤቱ በኒው ዮርክ በኢትዮጵያ ሰዓታት አቆጣጠር አርብ አመሻሽ ላይ ውይይቱን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የፀጥታው ምክር ቤት በየትኛው አጀንዳ ስር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚመክር እስካሁን ድረስ አልተገለጸም። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት፣ አሁን ወደ አጓራባች ክልሎች አፋር እና አማራ ዘልቆ ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውድመት እንደፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለወራት ያደረጉት ምርመራ አመልክቷል።
ምንጭ – ቢቢሲ