አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት አገራትን የአፍሪካ አገራት አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ከልቻሉ የተለያዩ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ግዛቷ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ሥርዓት እንዲታገዱ በፕሬዝዳንቷ ውሳኔ ተላለፈ።
የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሆኑት በአምባሳደር ካትሪን ታይ በኩል ይፋ በተደረገው በዚህ ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ነው ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትታገድ የተወሰነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ከአጎዋ ለማገድ ያሳለፈው ውሳኔ እንዳሳዘነው ገልጿል። ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳለው ይህ የአሜሪካ ውሳኔ በአጎዋ አማካኝነት ሲገኙ የነበሩ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታዎችን፣ ሴቶች እና ሕጻናትን ይጎዳል ብሏል።
ይህ የእገዳ ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በሁለት ወራት በኋላ ሲሆን ኢትዮጵያና ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት በዚህ ጊዜ ውስጥ “አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ከቻሉ በተጠቃሚነታቸው ይቀጥላሉ” ሲሉ ካተሪን ታይ አመልክተዋል። የአሜሪካ መንግሥት በአገሪቱ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን የአገሪቱ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚነትም ጥያቄ ውስጥ መውደቁ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ በመላክ ላይ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች እርምጃውን ተገቢ እንዳልሆነና በኢንዱስትሪዎቹ እየሰሩ የሚተዳደሩ ሰዎችን የሚጎዳ መሆኑን በመግለጽ ሲከራከሩ ቆይቷል።
ይህ ውሳኔ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደተላላፈ የገለጹት ባለሥልጣኗ የአሜሪካ አስተዳደር “እየሰፋ ባለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሌሎች ወገኖች ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው የሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች” በጽኑ እእንደሚያሳስበው ገልጸዋል። ውሳኔውን የተቃወመው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት አሜሪካ እንድታገዝ የጠየቀ ሲሆን፤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚሞክርን አማጺ የሚፋለመውን ሕዝብ መቅጣት የለባትም ብሏል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከዚህ የቀረጥ ነጻ ተጠቃሚነት የታገዱት በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄዶባቸው ሕገ መንግሥታዊ ከሆነው መንገድ ውጪ አሜሪካ ሥልጣን ተይዟል ያለቻቸው ጊኒ እና ማሊ ናቸው። አገራቱ እገዳው እንዲነሳላቸው የአሜሪካ መንግሥት የሚጠብቃቸውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው በመግለጫው ላይ ተመለክቷል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በርካታ ሰዎች ቀጥረው የሚሰሩ ፋብሪካዎች የተለያዩ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ሲልኩ ቆይተዋል።
በዚህ ውሳኔ ሳቢያ በሚፈጠር ጫና ፋብሪካዎቹ ሠራተኞች ሊቀንሱ ወይም ሥራ ሊያቆሙ እንደሚችሉ ስጋቶች አሉ። የአሜሪካ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር በተያኣዘ ከዚህ በፊት የቪዛ እገዳ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ባይደንም የተለያዩ እርማጀዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ውሳኔ መፈረማቸው ይታወሳል። አሜሪካ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ለአማጺያኑ ያደላና ፍትሃዊ ያልሆነ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥ በተደጋጋሚ ሲቃወም መቆቱ ይታወሳል።