የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ የውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መወሰኑን በፍትህ ሚኒስትሩ በዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው በዶክተር ለገሰ ቱሉ በኩል ነው ይፋ ያደረገው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገው “በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ” እንደሆነና ይህንንም አደጋ “በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ” ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስፈለጉ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ48 ሰዓታት ውስጥ መጽደቅ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ከዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በገመገመበት አስቸኳይ ስብሰባው ላይ ነው አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ የወሰነው ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የዚህ ውሳኔም ዋነኛ ዓላማ የአገሪቱ ዜጎች “በሽብር ቡድኑ የሚደርስባቸውን ጥቃት መመከት” መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን አስፈላጊነቱ ታይቶ ለተጨማሪ አራት ወራት ሊራዘም እንደሚችል ተጠቁሟል። የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚያስፈጽምና በበላይነት የሚመራ አካል ይቋቋማል ተብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የበላይነት የሚመራ ሲሆን ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ተገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው አካል ሁሉንም የፀጥታ አካላት ማዘዝና ማንቀሳቀስ የሚችል ሲሆን በአገሪቱ የሚገኙ “ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ አካል የማዘዝና የማሰማራት” ስልጣን ተሰጥቶታል ተብሏል።
ይህ አካል ሌሎች ዝርዝር የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣንና ኃላፊነቶች ተሰጡት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰዓት እላፊን ማወጅ፣ እንቅስቃሴዎችን መገደብ፣ በሽብር ከተፈረጀ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝና ተጠያቂ ማድረግ ይገኙበታል። ዛሬ እንደተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌውን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው፤ በቀላሉ እስከ ሦስት ዓመት የሚቀጣ ሲሆን ከፍ ሲል ደግሞ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ አስራት ሊቀጣ ይችላል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን ውሳኔውን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ እንዲጸድቅ ያስደርጋል። በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት አየስተስፋፋ መጥቶ በተለይ በአማራ ክልል የሚገኙት ደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እሁድ ዕለት ሁሉም አቅም ያለው ዜጋ የአማጺኑን ጥቃት እንዲመክት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲዘምት ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ነዋሪዎቻቸው ለዘመቻ እንዲከቱ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሁለት ቀናት ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ያላቸውን ጦር መሳሪያ እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል። የከተማዋ የሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀነአ ያደታ (ዶ/ር) በሁለት ቀናት ውስጥ በማያሳውቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቃቸውን የመዲናዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ በቀጣይ ቀናት በከተማዋ በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ