የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም አስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠየቁ።
የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊ ፒተር ሞውረር የኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተደረገ ያለው ጦርነት የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በየቀኑ እንዲጨምር እያደረገ ነው።
“በጦርነቱ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት መልዕክቱ ሁሌም ተመሳሳይ ነው። ለችግሩ አስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ከግጭት ያወጣናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ግጭቱ በፍጥነት ቢቆም እንኳን ከቀያቸው የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለብንም ሲሉም አሳስበዋል።
መንግሥት እና ህወሓት እርዳታ ሰጪዎችን ያለ ገደብ እንዲያሳልፉ ተጠየቀ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የተራድኦ ተቋም (ዩኤስኤድ) ኃላፊ ረዳት የሆኑት ሳራ ቻርልስ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም ህወሓት እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተረጂዎች ጋር እንዲደርሱ ገደብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል። ሳራ ቻርልስ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ዩኤስኤድ ባወጣው መግለጫ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓትም ይሁን የፌደራል መንግሥቱ እርዳታ ሰጪ ተቋሞች ያለ ምንም ገደብ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መንገድ እንዲከፍቱ ተጠይቋል።
ሳራ ቻርልስ ለአራት ቀናት በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ ከሰብአዊ እርዳታ ተቋማት እንዲሁም ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል። በአዲስ አበባ እና በባሕር ዳር የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያነጋገሩ ሲሆን፤ የእርዳታ ሰጪዎች ሕይወት አድን ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ መንግሥት በትግራይ ክልል የስልክ እና ኢንተርኔት እንዲሁም የባንክ አገልግሎትን እንዲመልስ ጠይቀዋል።
ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለ ምንም ገደብ እንዲያልፉ እና የሰብአዊ እርዳታ በረራ ቁጥር እንዲጨምርም ጠይቀዋል። የነዳጅ፣ የገንዘብ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
“ለወራት ያህል ነዳጅ፣ ገንዘብ እና የመድኃኒት አቅርቦት በኢትዮጵያ መንግሥት በመታገዱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሚሰጡትን ድጋፍ ለመቀነስ ተገደዋል። ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት መድኃኒት አልቆባቸዋል” ብለዋል።
በየብስ የሚሰጠው የእርዳታ አቅርቦት ካለው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰውም፤ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች በረራ ቁጥር እንዲጨመር አሳስበዋል።
የአሜሪካ የተራድኦ ተቋም በመግለጫው ረዳት ኃላፊዋ በጦርነቱ ሳቢያ ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተፈናቅለው ባሕር ዳር የሚገኙ ነዋሪዎችን አነጋግረዋል ብሏል። ተፈናቃዮቹ በሞት ስላጧቸው ቤተሰቦቻቸው፣ ምን አይነት ስቃይ እንዳሳለፉ እና ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም ለሳራ ቻርልስ እንደነገሯቸው ይጠቁማል።
አሁን በህወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች ቤተሰብ ያሏቸው ሰዎች ስለ ቤተሰቦቻቸው ደኅንት እንደሰጉም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ተነስቶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አንድ ዓመት የዘለቀው ጦርነት ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱን ሳራ ቻርልስ ተናግረዋል።
“ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ በተገቢ ሁኔታ እንዳይደርስ ያለው መሰናክል እንዲሁም በአፋር እና አማራ ክልሎች ተባብሶ የቀጠለው ውጊያ ባለፉት ሳምንታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል” ብለዋል።
ከዩኤስኤድ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከሌሎች የእርዳታ ተቋማት ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተገነዘቡት፤ የእርዳታ አቅርቦት ውስንነት ፈታኝ ሆኗል። ከዚህ ባሻገርም የእርዳታ ሰጪዎች ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሆነ እና በሁሉም ወገን ባሉ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ማስፈራራት እንደደረሰባቸውም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የምግብ ደኅንነት ጉዳይ፣ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑን የመጠበቅ ጉዳይ እና ወሲባዊ ጥቃትን በመከላከል ጉዳይ ከሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች ጋር ተወያይተዋል። ከተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ንግግር ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ መባረራቸው ተገቢ እንዳልሆነም ጠቁመዋል። የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ ለእርዳታ ወደ 663 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንዳወጣት የዩኤስኤድ መግለጫ ይጠቁማል።
ምንጭ – ቢቢሲ