በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አመራር ከመምጣቱ አንድ ዓመት በፊት ተፈጽሟል ከተባለ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (ፍትሕ ሚኒስቴር)፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተ፡፡

ክሱ የተመሠረተባቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ላይ የሕጓ አካል ያደረገቻቸውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ስቃይ ስምምነት (Convention Against Torture and Other Cruel Inhuman or Degrading Treatment or Punishment) አንቀጽ 1 እና 2(1)፣ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች (ICCPR) አንቀጽ (7) እና የአፍሪካ ሕዝቦችና ሰዎች መብት ሰነድ (Africa (Banjul) charter on Human and Peoples Rights) አንቀጽ  (5) እና (6)ን ድንጋጌዎች በመተላለፍ መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸውና በተቋማቱ ላይ ክስ የመሠረቱት አቶ ዮናስ ጋሻው ደመቀ የተባሉ ተበዳይ ሲሆኑ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው፣ ‹‹በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረሃል›› ተብለው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጥር 5 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ መሆኑም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ የስምምነት ድንጋጌዎች ተጥሰው ሰቅሎ (አንጠልጥሎ) በጎማ ዱላና ኤሌክትሪክ ገመድ ግርፋት፣ በሰውነት ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መልቀቅ (Electric Shocking) እንደተፈጸመባቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ መራመድ እንደማይችሉ፣ ለአዕምሮ ችግርና ለከፍተኛ የሥነ ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውንና መቶ በመቶ ቋሚ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በሙያቸው ሠርተው ያገኙት የነበረው ገቢ የባለቤታቸውን ጨምሮ መቋረጡንና ሌሎች አካላዊና የሥነ ልቦና ችግር እንደደረሰባቸውም ክሱ ያብራራል፡፡

የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ከሳሽ የተጠቀሱት ቋሚ ጉዳቶች የደረሱባቸው፣ በወንጀል ጉዳይ እንደሚፈለጉ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ፌዴራል ፖሊስ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረውን የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ድንጋጌን በመተላፍ፣ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአንድ ወር በላይ ታስረው እንዲቆዩ በማድረጉና ያልፈጸሙትን ወንጀል ‹‹ፈጽሜያለሁ›› ብለው እንደሚያምኑ፣ በተለያዩ የፖሊስ አባላት ተሰቅለው በመገረፋቸው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲለቀቅባቸው በመደረጉና ከሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ክስ ተመሥርቶባቸው ቅሊንጦ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ ከተወሰዱ በኋላም የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት እንዳይታከሙ በመከልከላቸው መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ለአራት ወራት ፍርድ ቤት ከተመላለሱ በኋላ ለጥርጣሬ የሚያበቃ ማስረጃ በመታጣቱ በነፃ ወይም በዋስ መለቀቅ ሲኖርባቸው፣ ፍርድ ቤቱ ምንም ሳይል መዝገቡን ዘግቶ ለስድስት ወራት ያህል በማዕከላዊ ሲገረፉና ሲደበደቡ ቆይተው፣ ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታቸውን እያሰማ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ባለመስጠቱ ጉዳቱ እየባሰ መምጣቱን ክሱ ይጠቁማል፡፡

በአጠቃላይ ከሳሽ የተያዙበት ሁኔታ ሕገወጥ መሆኑን ቢያመለክቱም እንዳልተመረመረላቸው፣ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸው አለመከበሩን፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት (ፍትሐዊ ዳኝነት) አለማግኘታቸውን ክሱ አብራርቶ፣ ከሕግ ውጭ መያዛቸው፣ በሕግ ከተፈቀደው ውጭ በምርመራ ክፍል ታስረው መቆየታቸው፣ የስቃይ ድርጊት ተፈጽሞባቸው ሳለ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ሕክምና እንዳያገኙ መከልከሉና በፍርድ ቤቶቹም ፍትሐዊ ዳኝነት ባለማግኘታቸው፣ የሚቆጣጠራቸው መንግሥት (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት) እና ተቋማቱ ተጠያቂ እንዲሆኑ ክሱ መቅረቡን የክስ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ተከሳሹ ባቀረቡት ክስ መሠረት ተከሳሽ ተቋማት በአጠቃላይ ለደረሰባቸው አዕምሯዊና አካላዊ ጉዳት 9,821,339 ብር የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከሳሽ ለደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉም ተቋማት ባልተነጣጠለ ሁኔታ ሙሉ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ እንዲወሰንላቸው፣ የተፈጸመባቸው ድብደባና ስቃይ፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕገ መንግሥቱ አካል ያደረገቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የጣሰ ነው እንዲባልላቸው፣ ተቋማቱ ሥልጣን ባለው አካል ትዕዛዝ በመስጠት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጽሙ በታዘዙ የፌዴራል ፖሊስና ማረሚያ ቤት ሠራተኞችና ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ክስ እንዲያቀርቡ እንዲታዘዝላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች አያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የስቃይ ተግባር (Torture) እንዳይፈጸምና ሥውር እስር (Incommunicado Detention) እንዲቀር ትዕዛዝ እንዲሰጥና ሌሎችም ትዛዝ እንዲሰጥላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት የፍትሐ ብሔር ክስ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *