1.2.  የሃሰተኛ መረጃዎች  የዝግጅት እና የስርጭት ሂደት

ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ሃቅን ለማጣራት እንዲችሉ የሚያግዝ ማጣቀሻ የቀጠለ. . . . . .

የሃሰተኛ  መረጃዎች   መነሻ   በአብዛኛው   የተደበቀና    በቀላሉ   ለመለየት የሚያስቸግር በመሆኑ መረጃዎች   ለሚያስከትሏቸው  መዘዞች   ተጠያቂ   አካላትን   ማግኘትና   በህግ   እንዲዳኙ   የማድረግ ሂደት  ቀላል   አይደለም፤  ምክንያቱም   ሃሰተኛ    አካውንቶችን    በመጠቀም   መረጃዎችን   በቀላሉ ማሰራጭት   ስለሚቻል።    ሃሰተኛ    መረጃዎችን   ያስተላለፉና    ያሰራጩ   አካላትን    ተከታትሎ የመያዝና  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ  ለማድረግ   አልፎ   አልፎ   አንዳንድ   እንቅስቃሴዎች  ቢኖሩም በቂ  እንዳልሆኑ  መግለጽ   ይቻላል።   ከዚህ     አንጻር   በብዙ  አገሮች   ያለው  ልምድም   ቢሆን   ያን ያክል  የሚያኮራ  አይመስልም። የመረጃዎች   ዝግጅትና ስርጭት ሂደት ምን ይመስላል  የሚለውን በመጠኑም ቢሆን  መዳሰስ  ያስፈልጋል።

የሃሰተኛ መረጃዎች  ዝግጅት  በግልሰብ ደረጃ ብቻ የተወሰነ  አይደለም።  የተለያዩ  አካላት በቡድን በመደራጀትና በመቀናጀት  እንዲሁም  ቦቶችን ጭምሮ በመጠቀም ሃሰተኛ  መረጃዎችን በስፋት በማሰራጨት     ከፍተኛ   ተጽዕኖ   የሚፈጥሩበት ሁኔታ   በተደጋጋሚ  ይስተዋላል። አንድ   የሆነ አላማ  ማሳካት  የፈለገ  ሰው  ወይም  ቡድን  የሃሰተኛ መረጃውን  ሃሳብ  ያመነጫል። ይህ     መረጃ ግቡን   ሊመታ   ይችላል   ተብሎ   በሚታሰብበት መልክ   ከተሰናዳ   በኋላ   በአዘጋጁ  ወይም   በሌላ ወገን  ወደ  ማህበራዊ   ሚዲያው  ይለቀቃል። በዚህ  መልክ  የተሰናዳው ሃሰተኛ   መረጃ  የማህበራዊ ሚዲያውን  ያጥለቀልቀውና መነጋገሪያ፣  ማደናገሪያ  ወይም  በመረጃው  አስተሳሰባቸው የተለወጡ አካላት ወደ አላስፈላጊ ሂደት እንዲገቡ መነሻ ይሆናቸዋል።

ነገር ግን የስነ-ተግባቦት ምሁራን እንደሚያስቀምጡት   ሁሉም    የሚለቀቅ   መረጃ   የታሰበለትን   ግብ   ላይመታ   ይችላል፡   ይህም አንድን   መረጃ  ወይም  መልዕከት ያዘጋጀው   አካል   መረጃውን   ከማዘጋጀት  የዘለለ  መረጃው  ምን አይነት  ውጤት   ሊያመጣ   እንደሚችል  ከመገመት  ውጭ   እርገጠኛ   መሆን  ስለማይችል  ነው። መረጃው  ከተላለፈ  በኋላ    በአንባቢዎች፣ ተመልካቾች እና  አድማጮች  በኩል የሚኖረው  አቀባበል የተለያየ  ስለሆነ  ነው። የሰው ልጆች ከየትኛውም  አቅጣጫ  የሚለቀቅን  መረጃ የሚረዱበትና የሚተረጉሙበት ሂደት  ባላቸው  የትምህርት ደረጃ፣  ባላቸው  ወይም  ከሌሎች  ሰዎች  በሰሟቸው ልምዶችና   ተሞክሮዎች፣  ለተለያዩ   ነገሮች  ባላቸው  ተጋላጭነት  እና  በመሳሰሉት  ላይ  በሰፊው የተመረኮዘ  ነው።

በመሆኑም   አንድን    ሃሰተኛ    መረጃ    ሰዎች    በሶስት    አይነት   መንገድ   ሊቀበሉት    ይችላሉ፡- የመጀመሪያው የተለቀቀውን   ሃሰተኛ   መረጃ  ያለምንም  ጥርጣሬ መረጃውን  አዘጋጅቶ  ያሰራጨው አካል  በሚፈልገው መንገድ የሚረዱና  የሚገነዘቡ  ሰዎች  አሉ  (Dominant/Prefered Reading)። እነዚህ   ሰዎች  አንድም  በመረጃው  አደገኝነት  ላይ  ቅንጣት  ጥርጣሬ ስለሌላቸው  (መረጃው  አደገኛ መሆኑን እያወቁ መረጃው የሚፈልጉትን አላማ እንዲመታላቸው ከመሻት  አንጻር)  አንድም የሚተላለፈው   መረጃ  የሚያደርሰውን  መዘዝ   ካለመረዳት   መረጃውን   በማጋራት  በርካታ   አካላት ጋር  እንዲደርስ   የማድረግ ስራ  ይሰራሉ።

በሁለተኛው ረድፍ  የሚገኙ  ሰዎች  የተለቀቀውን  መረጃ ሙሉ   በሙሉ  ከመቀበል ይልቅ  የተወሰነውን የመረጃው   ክፍል  የመቀበልና ሌላውን  የመረጃው ክፍል  ያለመቀበል/ውድቅ/ የሚያደርጉ ናቸው(  Negotiated Reading)። በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙት ሰዎች   ደግሞ   በመጀመሪያው  ረድፍ   ከሚገኙት  በተቃራኒ  የቆሙ   ናቸው።   የተለቀቀውን   መረጃ ሙሉ  በሙሉ ውድቅ የሚያደርጉ ናቸው /Oppositional Reading/። መረጃውን  ሙሉ  በሙሉ በሚቀበሉትና  በሚቃሙት  መካከል   አንድ   የሚያመሳስላቸው  ነገር   አለ   ፤  ይህም   አንዳቸው መረጃውን   ደግፈው   ሲያጋሩና  ሲያስተላልፉ ሌሎቹ  ደግሞ   ይኸውን   መረጃ  ትክክል  እንዳልሆነ በመግለጽና  በመቃወም   ማጋራታቸው  ነው።  በሁለተኛው  ረድፍ   የሚገኙትም  ቢሆን   መረጃውን ከማጋራት ላይቆጠቡ  ይችላሉ።    በዚህ  ሁኔታ አንድ  ሃሰተኛ  መረጃ  በፍጥነት እየተላለፈ  ለበርካታ ምናልባትም በወል   ቁጥራቸው   ወደማይታወቅ ታዳሚያን     እንዲደርስ   ይደረጋል።

1.3.  የሃሰተኛ መረጃ ተዋናዮች

የሃሰተኛ   መረጃዎችን  በማዘጋጀትና  በማሰራጨት  ረገድ   የተለያዩ    አካላት   ተሳታፊ    ናቸው። መረጃውን   ከማሰራጨት  አንጻር   በተለያየ   የእውቀትና  የልምድ  ደረጃ     ላይ   የሚገኙ    አካላት በመደገፍና  በመቃወም   ሊያስተላልፉት  እንደሚችሉ   ከፍ   ብሎ   በተቀመጠው  ርዕሰ-ጉዳይ  ላይ በደንብ  ተብራርቷል።  በመሆኑም  ሃሰተኛ   መረጃውን   በማሰራጭት  ከመረጃው   አዘጋጆች   ውጭ ያሉት  ሰዎች  ሚና  ከፍተኛ  መሆኑን  በመጥቀስ  ወደ  ዋናዎቹ ተዋናዮች  ማለፍ  ተገቢ  ይሆናል።

  •  ግለሰቦች፡-   አንዳንድ   ግለሰቦች   ሃሰተኛ   መረጃ   አቀነባብረው   በማሰራጨት  ትኩረትን   ለማግኘት ይሞክራሉ።  በዚህ   እንቅስቃሴ   ውስጥ   የሚሳተፉ  ግለሰቦች   በተጠቃሚዎች መካከል  ልዩነትን የሚፈጥር እና  ስሜት  ቀስቃሽ  የሆኑ መረጃ  በመልቀቅ ትኩረትን  ለማግኘት  ጥረት   የሚያደርጉ ናቸው።
  • ለገንዘብ   የሚሰሩ    አካላት፡-    እነዚህ    አካላት   በዋናነት  ለሚያዘጋጁት  ይዘት    በርካታ    ተጠቃሚ በማፍራት በሂደት  ማስታወቂያዎችን እና  ስፖንሰር በመሳብ  ትርፍ ማግኘት  የሚፈልጉ  ናቸው። በዚህ  ስራ  የሚሳተፉ አካላት    የሚያዘጋጁት መረጃ  ዋና  አለማ  የታዳሚ   ቁጥር  በመጨመር  ገቢ ማስገኘት  እስከሆነ   ድረስ  ወደ  ማህበራዊ   ሚዲያው  የሚለቀቀው   መረጃ  ችግር  ያለበትና   ሰዎችን የሚያሳስት ይሆናል።  ከላይ   በ  1.1   ስር   ከተዘረዘሩት  የተወሰኑትን  እንደ   ሁኔታው  ተጠቅሞ መረጃን  በማዘጋጀት  የተጠቃሚ  ቁጥር   በመጨመር  ከሚገኘው  ገንዘብ  ለመጠቀም   ቀንና  ለሊት የሚተጉ  የሃሰተኛ መረጃ  ፋብሪካዎች  በርካታ  ናቸው።  ነገር  ግን  ሁሉንም  አካላት  የሃሰተኛ  መረጃ አምራቾች  አድርጎ   መውሰድ  ደግሞ   ትልቅ   ስህትተ   ነው፡   ምክንያቱም  በከፍተኛ   ጥረትና ትጋት እውነተኛ ይዘቶችን አዘጋጅተው በማህበራዊና በኦን ላይ ሚዲያ ላይ በመጫን  ገንዘብ ለማግኘት የሚታትሩት በርካቶች  ስለሆኑ።
  •  አክቲቪስቶች እና ብሎገሮች፡- የተለያየ  ዓላማን አንግቦው በየጎራው  ተሰልፈው በታዳሚያን  አመለካከት ላይ  ተጽዕኖ  ለመፍጠር የሚሰሩ  ናቸው።  አነዚህ  አካላት  በርካታ  ቁጥር  ያለው  የማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ ያላቸው ከመሆኑ አንጻር  በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች  ላይ የሚያስተላልፉት የተዛባ መረጃ የሚፈጥረው  ተጽዕኖ   ቀላል   እንዳልሆነ  መግለጽ   ይቻላል።      ነገር   ግን   ሁሉም   አክቲቪስቶችና ብሎገሮች  ሃሰተኛ   መረጃን  አንደሚያስተላልፉ አድረጎ  መረዳት  ደግሞ  ስህተት   ነው።
  • ፖለቲከኞች    ፣  መንግስት እና   የተለየ    የፖለቲካ  ፍላጎት    ያላቸው   ቡድኖች:-   ሃሰተኛ    መረጃ ከማሰራጨት አንጻር  ከፍተኛ  ሚና  ይኖራቸዋል። የዘመኑ የፖለቲካ ትግል በፊት  ለፊት  የመድረክ ክርክር ብቻ ሳይወሰን ዘመኑ  ያፈራውን  የሰነ-ተግባቦት ዘዴ  በመጠቀም  ጭምር  የሚካሄድ  ነው። ፖለቲከኞች  በተለያዩ  የማህበራዊ ሚዲያዎች  ላይ ሃሳባቸውን እየጻፉ  በቀላሉ ለተከታዮቻቸው  እና ለማህበራዊ   ሚዲያ  ታዳሚያን   ያሥተላልፋሉ። ግራም-  ነፈሰ  ቀኝ የፖለቲካ ስራ  አሻጥርና  ብዙ ቁማሮች  ያሉበት  በመሆኑ ፖለቲከኞች  የሚጽፏቸው  መረጃዎች  የአንድ  ወገን  ፍላጎትና አተያይን የሚገልጹ በመሆኑ ሰዎችን  የማሳሳት እድላቸው  ከፍተኛ  ነው፤ በተለይ  ደግሞ  ተከታዮቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን።

የመንግስት  ባለስልጣናትም  ቢሆን   ያልተሰራውን  እንደተሰራ(አጋነው)  የሚያቀርቡ፣  ዛሬ የተናገሩትን  ነገ  የሚሽሩ፣  ህዝብን   በሃሰተኛ  መረጃ   የሚሸነግሉ፣ የተቋሞቻቸውን   ስምና   ዝና ለመጠበቅ   ሲሉ   ትክክለኛ   መረጃ   በመስጠት  ፈንታ   ነገሩን   አድበስብሰው   ማለፍን   የሚመርጡ በርካቶች በመሆናቸው ሃሰተኛ መረጃዎችን በማዘጋጀትና በተለያየ  መልኩ አንዳንዴም  በግላቸው የማህበራዊ  ሚዲያ   ሰራዊት   አማካኝነት   በማስተላለፍ   ተሳትፏቸው  የላቀ  ነው።   በተጨማሪም የተለያየ   የፖለቲካ  ፍላጎት   ያላቸው  በግልጽ  በፖለቲካ   የመጫወቻ   ሜዳው  ላይ  የማይታዩ  እና ከመጋረጃ  ጀርባ  ሆነው   የሚታገሉ  አካላትንም   ጭምር   መጥቀስ  ያስፈልጋል።  አንዱ   የጻፈውን መረጃ   እረስ   በእርስ   በመቀባበል  እና   በመወዳደስ    የጋራ  አጀንዳ   አድርገው  በብዙዎች    ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው   የሚሰሩ  ብዙዎች  ናቸው፤ በዚህ  ሂደትም   ጥሬውን   ከብስሉ  በመቀላቀል እና  የሚያስተላልፉት መረጃ  ሊያስከትል የሚችለውን  መዘዝ  ከእቁብ  ሳይቆጥሩ ህዝብን  በሃሰተኛ መረጃ የሚያደነዝዙ ሰዎች  ቁጥር  የሚናቅ  አይደለም።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *