በሁለት ቀናት ልዩነት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ።
ቢቢሲ ከዓይን እማኞች እንዳጣራው ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ከአራት ሰዓት በኋላ የተፈጸመው የአየር ድብዳባ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በተባለው ተቋም ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። ሮይተርስ የዜና ወኪል በክልሉ የሚገኝ ቴሌቪዥን ጣቢያን እንዲሁም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ደግሞ የረድኤት ተቋማት ምንጮችን ጠቅሰው የአየር ጥቃት ስለመፈጸሙ ዘግበዋል።
ቢቢሲ ስለአየር ጥቃቱ ከአገር መከላከያ ቃል አቀባይ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። በተመሳሳይ ሮይተርስ የዜና ወኪል በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናትን አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት አመልክቷል። ይሁን እንጂ የመንግሥት የወቅታዊ መረጃ አጣሪ በትዊተር ገጹ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ ዒላማ የተደረጉትም የህወሓት የጦር መሳሪያ ማምረቻ እና መጠገኛ ስፍራዎች ናቸው ብሏል።
መረጃ አጣሪ ማዕከሉ ስለአየር ጥቃቱ ይፋ ባደረገው መረጃ የተካሄዱት ኦፕሬሽኖች ዒላማ ያደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው ብሏል። ጨምሮም “የሽብር ድርጅቱ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ለመሸሸግ የሚጠቀምባቸውን እና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ያለመ ነው” ብሏል።
በአየር ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ዝርዝርን በተመለከተ አስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ የለም። በጥቃቱ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው አንዲት ነፍሰጡር ሴትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአይደር የሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ኃላፊ ገልጸው ከመካከላቸው አምስቱ በሆስፒታሉ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንና ሦስቱ መቀለ ሆስፒታል መግባታቸውን ለቢቢሲ ትግረኛ ተናግረዋል።
በህወሓት የሚተዳደረው ቴሌቪዥን ጣቢያም ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ተዋጊ ጀቶች በመቀለ ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸማቸውን ጥቃቱን ተከትሎ ዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪም በመቀለ ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸሙን ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ክንደያ ገብረሕይወት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።
የአየር ድበደባውን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በስፋት እየወጡ ይገኛሉ። ቢቢሲ የእነዚህን ምስሎች ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልቻለም። የዛሬው የአየር ጥቃት ኢላማ ነበሩ ከተባሉት አንዱ መስፍን ኢንደስቱሪያል ኢንጂነሪንግ ኤፈርት የተባለው ኢንዶውመንት ፈንድ አካል በመቀለ ከተማ የሚገኝ ግዙፉ ተቋም ነው።
ምንጮች ረቡዕ በቀናት ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተፈጽሟል በተባለው የአየር ጥቃት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም እስካሁን ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በአየር ጥቃቱ መኖሪያ ስፍራዎች ዒላማ ተደርገዋል ሲሉ ከሰዋል።

ከትናንት በስቲያ ሰኞ በተመሳሳይ የኢትጵያ አየር ኃይል በመቀለ የአየር ድበደባ ፈጽሞ እንደነበረ ይታወሳል። በዚህ የአየር ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ስለማለፉ የህወሓት ባለስልጣን፣ የረድኤት ሠራተኛ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጸው ነበር። ይህን የአየር ድበደባ በተመለከተ የመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ሐሰት ነው ቢሉም ዘግይቶ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አየር ኃይሉ ድበደባ መፈጸሙን ዘግቧል ነበር።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዘገባው የአየር ኃይሉ ዒላማዎች ህወሓት ይጠቀምባቸዋል ያላቸው የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች መሆናቸውን እና በጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል ብሏል። በሰኞው ዕለት የአየር ጥቃት በተፈጸመበት ጊዜ “ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ ይህም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል” ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቦ ነበር።
ምንጭ – ቢቢሲ