በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን፣ በአምባሰል ወረዳ በምትገኘው ውጫሌ ከተማ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በሽብርተኛ ቡድንነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር እያካሄደ ያለው ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ሲሆን ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክሎች ተስፋፍቶ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ መልሶ ባገረሸው ጦርነት ወቅት የህወሓት ኃይሎች በውጫሌና በጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት አሳውቋል።

የአምባሰል ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሀብቴ መለሰ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የህወሓት አማጽያን በውጫሌ ከተማ ላይ በፈጸሙት የከባድ መሣሪያ ጥቃት ሁለት ወንድማማቾችን ጨምሮ በአጠቃላይ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አልፏል። “እሁድ ዕለት ወደ ከተማዋ ከባድ መሣሪያ ተተኩሶ የዘጠኝ ሰው ሕይወት አልፏል። ከአንድ ቤት ሁለት ወንድማማቾች ሞተዋል። መደበኛ ሥራ ላይ የነበሩ እና በመሸሽ ላይ የነበሩም ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል” ብለዋል።

በተጨማሪም አራት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው ሕክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኙም አክለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ አማጺያኑ በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎችን ዒላማ በማድረግ “ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተቀባይነት የሌለው ጥቃት” ፈጽመዋል ብሏል።

አዲስ የተዋቀረው የኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የህወሓት ኃይሎች በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ ፈጸሙት ባሉት ጥቃት ከ30 በላይ ንጹኀን ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶችን መፈናቀላቸውን ተናግረዋል። በጦርነቱ በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከአምባሰል እንዲሁም በዙሪያዋ ካሉ ከሌሎች ወረዳዎች ጦርነቱን በመሸሽ ብዙዎች ወደ ደሴ ከተማ መሰደዳቸውን አቶ ሀብቴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ነዋሪዎች አሁንም እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ እና በደሴ ዘመድ ወይም ጓደኛ የሌላቸው ሰዎች በረንዳ ላይ እንደወደቁ ተናግረዋል። እሁድ ጥቅምት 07/2014 ዓ.ም. የህወሓት ኃይሎች ወደ አካባቢው መግባትን ተከትሎ ብዙ ነዋሪዎች ሸሽተው እንደወጡ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አስረድተዋል። አቶ ሀብቴ ከባድ መሣሪያው የተተኮሰበትን አቅጣጫ እንዲሁም ሰዓት በማጣቀስ “ከባድ መሣሪያው የተተኮሰው በህወሓት ነው” ብለዋል።

ህወሓትም በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው ጥቃት እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም። በተለይም ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደ አዲስ ተጠናክሮ በተጀመረው የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ውጊያ ሳቢያ፣ ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እና ጉዳትም እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል። ከሰሜን ወሎ ዞን፣ ሀብሩ ወረዳ ጦርነቱን ሸሽተው ከአምስት ልጆቻቸው ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ተጠልለው የሚገኙት የዓይን እማኝ፤ ሰዎች እንደተገደሉ እና የቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ተናግረዋል።

“በሀመሮ 43 ቤት ተቃጥሏል። ሀብሩ ውስጥ የተረፈ የለም። ይሄን ያህል ነው ለማለት አልችልም። ሰውም ሞቷል። አብረን እየሸሸን ሳለን የሞቱ አይቻለሁ። ሰው እንደ ቅጠል ነው የረገፈው” ሲሉ የተፈጠረውን አስረድተዋል። የእርሳቸው ቤት ባይቃጠልም የአባታቸው እና የወንድሞቻቸው መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ ተናግረዋል። በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ መጠለያ ያላገኙ ሰዎች እንዳሉ ገልጸው፤ “መግቢያ የሌለው በረንዳ ነው ያለው። ዝም ብሎ ተበታትኗል። የማይተዋወቀውም እንድ ላይ ተደባልቋል” በማለት ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

አብዛኛው ቤተሰብ እንደተለያየ እና ተፈላልገው የተገናኙት አንድ ላይ እንደሚገኙም አክለዋል። ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥቱ ባወጣው መግለጫ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ግጭት “የጫረው ህወሓት ነው” ቢልም ህወሓት በበኩሉ በአማራ እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ ግንባሮች መንግሥት ጥቃት እንደከፈተበት አስታውቋል። አንድ ዓመት ሊሞላው የሳምንታት ዕድሜ በቀረው ይህ ጦርነት ላለፉት ጥቂት ሳምንታት በአንጻራዊነት ጋብ ብሎ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ዳግመኛ ተፋፍሟል።

በጦርነቱ ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ሚሊዮኖች ደግሞ በረሃብ ስጋት ውስጥ እንዳሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲገቡ ጫና ማሳደሩን ቀጥሏል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *