የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰኞ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም በመቀለ ከተማ በተመረጡ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ።

አየር ኃይሉ ፈጸምኩት ባለው የአየር ድብደባ ህወሓት ይጠቀምባቸዋል ባላቸው የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንና በጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል። የፌደራሉ መንግሥት መቀለ ከተማ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን አንድ የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንዲሁም የእርዳታ ሠራተኛና አንድ ዲፕሎማት ደግሞ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

ሰኞ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም በመቀለ ከተማ የአየር ድብደባ መፈጸሙን በክልሉ የሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፤ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ክንደያ ገብረሕይወትም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ክንደያ የአየር ድብደባው የተፈጸመው በመቀለ ከተማ በሚገኙ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጠዋት 3 ሰዓት ተኩል ከከተማዋ ወጣ ብሎ ሃሬና ወይም መሰቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና አዲሃቂ ተብሎ በሚጠራው የገበያ አካባቢ ነው ብለዋል።

ጨምረውም በጥቃቶቹ ሦስት ሰዎች መገደላቸውንና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል። አየር ኃይሉ በበኩሉ የአየር ጥቃቱ ዒላማ የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች መሆናቸውን እና በጥቃቱ “ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ ይህም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል” ብሏል። ቢቢሲ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም። ትናንት ከሰዓት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ምንም አይነት ጥቃት አልፈጸመም ሲሉ ተናግረው ነበር። “የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን የራሱ ከተማ በሆነችው መቀለ ላይ ጥቃት ይፈጽማል?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ጨምረውም “መንግሥት ሳይሆን አሸባሪዎች ናቸው ሰላማዊ ሰዎች የሚኖሩባቸውን ከተሞች የሚያጠቁት” በማለት የህወሓት አማጺያን በአጎራባች የአፋር ክልል ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ ከሰዋል። ሮይተርስ ያናገራቸው አንድ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ እና ዲፕሎማትም በመቀለ ከተማ የአየር ጥቃት እንደነበር ገልጸዋል። በክስተቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ዝርዝርን በተመለከተ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውና ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከባድ ጉዳትን አስከትሏል። ከሰኔ ማብቂያ ጀምሮ በተለይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መልሶ ያገረሸው ውጊያ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተለያዩ ስፍራዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ ከአካባቢዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ