1.1. የሃሰተኛ መረጃ አይነቶች
ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ሃቅን ለማጣራት እንዲችሉ የሚያግዝ ማጣቀሻ የቀጠለ. . . . . .
ከላይ ሶስቱ ዋና ዋና የሃሰተኛና ጎጂ መረጃዎች የተጠቀሱት የመረጃዎችን አላማ መሰረት በማድረግ ሲሆን የሃሰተኛ መረጃዎችን አይነት ደግሞ ከዘህ በታች ዘርዘር አደርጎ መመልከት ተገቢ ነው።
ሀ፣ የምጸት መረጃዎች (Satire and Parody) ፡ ምጸት አንድን ሃሳብ፣ ስራ ወይም ሰው አስቂኝ በሆነ መልኩ /ዘና እያደረገ/ የመተቸት ዘዴን ይገልጻል።ፓረዲ / Parody / ደግሞ የአንድን ታዋቂ ሰው የአነጋገር ወይም የአጻጻፍ ዘይቤ በአስቂኝ መንግድ መኮረጅ ነው። እነዚህ መረጃዎች በዋናነት የምናባዊ ፈጠራ ይዘት ያላቸው እና ተገቢነት የሌላቸውን ስራዎችና ባህሪያት ለማጋለጥ ወይም ለመንቀፍ የሚጠቅሙ ቢሆኑም በግልጽ የምጸት መረጃዎች መሆናቸው ካልታወቀ በስተቀር ካለው የመረጃ መጥለቅለቅ ጋር ተዳምረው ሰዎችን የማሳሳት ወይም ግራ የማጋባት ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ።
ከዚህ በታች የቀረበው ምሳሌም እንዴት የታዋቂ ሰዎችን የአጻጻፍ ዘይቤ በመኮረጅ አንባቢያንን ማደናገር እንደሚቻል በገልጽ የሚያሳይ ነው። ከታች በምስሉ የምትመለከቱት የጤና ሚንስትሯ የተከበሩ ወ/ሮ ሊያ ታደሰ የተናገሩት በማስመሰል በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በመጠቀም አንባቢያንን ለማሳሳት የተቀመጠ መልዕክት ነው። ይህ አሳሳች መልዕክት በፌደራል መንግስቱና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መካከል ጦርነት ከተከሰተ በኋላ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ብቅ ማለቱን ተከትሎ ምን ያክል ጊዜ ሰዎች እንዳጋሩት እና እንደወደዱት የሚገልጽ መረጃ ከምስሉ ታች ይታያል። የጤና ሚንስትሯ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ደጋግመው የሚገልጹትን ሃሳብ በመወስድ ሰዎችን ለማምታታት የተደረገ ሙከራ ነው። በዚህ ሂደትም ሚንስትሯ በወቅቱ የነበረውን የጦርነት ሁኔታ እንደማያውቁ አድርጎ በመሳል የሚንስትሯን ስምና ዝና ጥላሸት ለመቀባት እና ለአላስፈላጊ ትችቶች እንዲጋለጡ ለማድረግ የተደረገ ሙከራ ነው።
ለ፣ ይዘቱና አርዕስቱ/ ምስሎች/ የማይገናኙበት መረጃ (False connection) ፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚዘዋወሩ ምስሎች ወይም አርዕስቶች ከቀረበው ይዘት አንጻር ምንም አይነት ግንኙነት ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ በዩቲውብ ላይ የሚለጠፈው ምስል ወይም አርዕስት እና የሚቀርበው ወሬ/ትረካ/ በፍጹም የማይገናኙ ይሆናሉ። በፌስቡክና በሌሎችም የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመግቢያቸው የሚጠቀሙበት አርዕስት/ምስል/ ቀጥሎ ከቀረበው ይዘት ጋር የማይገናኝ ይሆናል። ይህ አይነቱ የማጭበርበሪያ አሰራር በስፋት በፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ በዩቲውብና በመሳሰሉት ላይ ይስተዋላል። ሰዎች የቀረበውን ይዘት እንዲያነቡት /እንዲያደምጡት/ ለማድረግ በጣም ቀልብን የሚገዛና ትኩረትን የሚስብ አርዕስት /ምስል/ የመጠቀም ሁኔታ በእጅጉ የተለመደ ነው። በመሆኑም ይዘቱንና አርዕስቱን/ምስሉን/ አዛምደው በቅጡ አንብበው ሳይረዱ የተጻፈውን ካላይ በማየት ብቻ መረጃውን የሚያሰራጩ በርካቶች ናቸው። እንደዚህ አይነት አሰራር የአንባቢና የተመልካች ቁጥር ለመጨመር የሚደረግ ጎጂ አሰራር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ከዚህ በታች የምተመለከቱት ምስል በፌደራል መንግስት እና ትግራይ ክልል መካከል በ2013 ዓ/ም በተፈጠረው ግጭት/ጦርነት/ ወቅት የትግራይ ሃይሎች መተው የጣሉት የፌደራል መንግስት የጦር አውሮፕላን ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያው በስፋት ሲዘዋወር እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።
በልምምድ ላይ የነበረ አንድ የኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላን በጥቅምት 2012 ዓ/ም በቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰ ሲሆን የአሰልጣኙና ሰልጣኙ ህይዎት ማለፉ ይታወሳል።
ሐ፣ አሳሳች ይዘት (misleading content) ፡ ከአንድ ጽሁፍ/ንግግር/ ላይ የተወሰነውን ክፍል ቆርጦ በማወጣት/በመውሰድ/ሌላ ትርጉም እና ግንዛቤ እንዲያዝበት አድርጎ ማዘጋጀት ነው። ይህም በአንድ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀውን ሙሉ ጽሁፉ በማንበብ /ሙሉ ንግግር በማድመጥ/ ከሚያዘው ግንዛቤ የተለየ እንዲሆን ስለሚያደርገው ሰዎችን የሚያሳስትና ተገቢ ያልሆነ አረዳድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ ጥቅሶችን ወይም ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን መርጦ በመጠቀም አንድን ርዕሰ-ጉዳይ ወይም ሰው በተለየ መልኩ ትርጉም እንዲሰጠው የማድረግ ሂደት ነው። ምስሎችን በመቆራረጥ በተመሳሳይ ሁኔታ የማሳሳት ስራዎች ይሰራሉ።
መ፣ ከአውድ ውጭ የሚወሰድ መረጃ /out of context/ ፡ አውድ ነገሮችን ለመረዳት ከፍተኛ እድል ይሰጣል። አንድን ሃሳብ ከቀረበበት ወይም ከተነገረበት ሁኔታ/አውድ/ ውጭ በመወስድ አሳሳች መልዕክት የመፍጠር ሂደት ነው። በመሆኑም ሃሳቡ ከአውዱ ተነጥሎ ስለሚቀርብ በመጀመሪያ ከያዘው ትርጉም የተለየ ትርጉም ይኖረዋል። ለምሳሌ በ2012 ዓ/ም በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በተፈጠሩት ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የጥቃቱን እና የሟቾችን ሁኔታ ለመግለጽ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ በሁቶዎች የተገደሉትን የቱቲስዎች እስከሬን ሲጠቀሙት እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። ነገር ግን በኢትዮጵያና በሩዋንዳ የነበረው ሁኔታ ፈጽሞ የተለያየ ነው። በሩዋንዳ የተከሰተው ዘርን መሰረት ያደረገውን ጭፍጨፋ የሚያሳየው ምስል እውነት ቢሆንም በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ክስተት ለመግለጽ መስሎ ጥቅም ላይ የዋለበት ሁኔታ ግን አውዱን ያላገናዘበ ነው።
ሠ፣ ተመሳስሎ የሚዘጋጁ/ አስመሳይ/ ይዘቶች/ Imposter Content/: ይህ ታዋቂ የጥበብ ሰዎችን፣ ባለስልጣናትን፣ ተቋማት፣ ጋዜጠኞችንና የመሳሰሉትን አካላት ስም፣ ምስል፣ የድርጅት፣ የመሳሰሉትን በመጠቀም የተለያዩ አሳሳች ይዘቶችን የማዘጋጀት ሂደትን ይገልጻል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ተመሳስለው የተከፈቱ ድረ-ገጾችን፣ የግልና የድርጅት የማህበራዊ ሚዲያዎችን ለማዘጋት ሲጥሩ/ ሲጠይቁ/ ወይም የእነሱ እንዳልሆኑ ሲገልጹ ማየት የተለመደ ክስተት ነው።
ረ፣ የተቀነባበረ ይዘት/Manipulated Content/፤ እውነተኛ መረጃን/ምስልን/ በመጠቀም ለማጭበርበርና ለማታለል በሚያስችል መልኩ ይዘትን አቀነባብሮ ማቅረብ ነው። ለምሳሌ ከዚህ በታች የሚታዩት ሁለት ምስሎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከእሁሮ ኬንያታ ጋር ያደረጉትን ጉብኝት የሚያሳየውን ምስል በመነካካት ጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያደረጉት አስመስሎ ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል።
ያለው የተሳሳተ ሲሆን ከታች የሚታየው የ “✓”ምልክት ያለው ግን ትክክለኛ ነው።
ሰ፣ ሃሰተኛ የፈጠራ ይዘት/fabricated content/፡ ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሃሰተኛ መረጃን/ይዘትን/ አዘጋጅቶ በማህበራዊ ሚዲያውና በተለያዩ ሃሰተኛ ድረ-ገጾች ላይ ማቅረብን ይገልጻል። በመሆኑም የተለያዩ ጽሁፎች፣ ማስታዎቂያዎች፣ የጽሁፍ-ሰሌዳዎች፣ አጫጭር ቪዲዮዎች በሃሰተኛ መረጃዎች ላይ ተመስርተው በማህበራዊ ሚዲያውና በተለያዩ ሃሰተኛ ድረ-ገጾች ላይ ሊለቀቁ ይችላሉ። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጉዳት ስላጋጠማቸው ለህክምና ወደ ውጭ አገር ሄደዋል የሚል ጽሁፍ በማህበራዊ ሚዲያው መናፈሱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ደህንነት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ የሃሰት እንደሆነ ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ለማሳሰብ እንወዳለን” የሚል ምላሽ እንዲሰጥበት አድርጓል። ይህ ሃሰተኛ መረጃ በጥር ወር 2013 ዓ/ም አካባቢ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ብቅ ያለ ሲሆን በየጊዜው ለሚከሰተው የሃሰተኛ መረጃ አንድ ማሳያ አድርጎ መወስድ ይቻላል። ይህ ምሳሌ ሙሉ በሙሉ የፈጠራ መረጃ ሲሆን በጊዜው መደናገርን ፈጥሮ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።